
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።
ሽልማት እና እውቅና የተሰጣቸው ተማሪዎች ይህንን ውጤት ያስመዘገቡት ሁሉም ነገር በተስተካከለለት የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ሳይኾን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ሁሉ አልፈው እንደኾነ ገልጸዋል። መሠረተ ልማታቸው በወደሙ ትምህርት ቤቶች አልፈው እንዲኹም ባልተሟላ የመማሪያ ቁሳቁስ ተምረው ይህንን ውጤት ማስመዝገባቸውን ነው የተናገሩት።
ተማሪዎች እንደገለጹት በተለይም ፈተና በሚወስዱበት ወቅት የተቀሰቀሰው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ ተጽእኖ ያለው እና የብርቱ ብርቱ መኾንን የሚጠይቅ ነበር።
ለፈተና እንደተቀመጡ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ሌላ ያልተዘጋጁበት ድንገቴ ፈተና ኾኖባቸዋል።
ይህ የሰላም መደፍረስ ችግር ለበርካቶች የትምህርት ውጤት መቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አይካድም። በጽናት አልፈው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ደግሞ ተሸላሚዎች ኾነዋል።
“ተምረን ጥሩ ውጤት ማምጣት፣ ተወዳድረን ማሸነፍ እንጅ እየተተኮሰብን ወደኋላ መቅረትን አንሻም” የተሸላሚ ብርቱ ተማሪዎች ሀሳብ ነው። ተወዳዳሪ ለመኾን ሰላም ላቅ ያለ ሚና አለው። ተወዳዳሪ ትውልድ እንዲኖር ከተፈለገ ሰላምን ማስፈን ግድ ይላል ማለት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!