“በጎ ምክር የሰማ ይሻገራል፣ ምክርም ያልሰማ ይወድቃል”

48

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎ ምክር ሀገር ትገነባለቸ፤ በጎ ምክር ጥልን ታስቀራለች፤ ከመከራ ታሻግራለች፤ የደም መፍሰስን፣ የአጥንት መከስከስን ታስቆማለች፤ በጎ ምክር ሰላምን ታመጣለች፤ ጥልና ጥላቻን ታርቃለች፤ ፍቅርን ታነግሳለች፤ መዋደድን ታበረታለች፡፡

ደጋጎች በጎ ምክርን እየመከሩ ሀገር አጽንተዋል፤  ብልሆች አንተም ተው አንተም ተው እያሉ ጠብን ገድለዋል፤ ለግድያ የሚፈላለጉትን አስታርቀዋል፡፡ ጠብ በነገሠባት ምድር ፍቅርን ዘርተዋል፤ ክፉ ነገር በነገሠባት ቀዬ መልካምን አድርገዋል፡፡ እሾህ እየነቀሉ፣ ፍሬ ተክለዋል፡፡

በጎ ምክርን ያልሰማ ይወድቃል፤ ከጥላቻ እየቀረበ ከፍቅር ይርቃል፤ ደግ መካሪ እና ጆሮ የሚሰጥ ተመካሪ ባለባት ምድር ጠብ አይኖርም፤ ሰላም አይጠፋም፤ መዋደድ አያድፍም፤ ደግ መካሪዎች ሲጠፉ ወይንም ሰሚ አጥተው ዝም ባሉ ጊዜ ግን የከፋችው ሁሉ ትመጣለች፡፡ ምድር በሁካታና በብጥብጥ ትታመሳለች፤ በወንድማማቾች ደም ትታጠባለች፡፡

የሀገሬው ሰው ምንም የከፋ ነገር ቢመጣ ከሽማግሌ እና ከሽምግልና አያልፍም ይላል፡፡ ሽማግሌ በብልሃቱ የተቀደደን ሰማይ ይሰፋል፣ የጠበበን ሀገር ያሰፋል፣ ደም የተቃቡትን አስታርቆ በመተማመን ያስተቃቅፋልና፡፡ ለዚያም ይመስላል

“ተውት እንዳሻው የመጠው ይምጣ
ከሽማግሌ ከእርቅም አይወጣ”  የሚሉት፡፡

የሀገሬው ሰው የመጣው ቢመጣ፣ የፈለገው ነገር ቢሆን ከሽማግሌ የሚወጣ፣ ሽማግሌ የማይፈታው ነገር እንደሌለ ያምናል፡፡  በዚህም እምነቱ እየተገዛ ወዮ ያስባሉ ችግሮችን እየፈታ፣ ጥልን በፍቅር እየረታ ለዘመናት ኖሯል፡፡ የከበረች ሀገር፣ እስከ ከበረ ታሪኳ አስረክቧል፡፡

ጥል በበዛባት ቀዬ የሽማግሌ በትር ሲቆምባት ሰላም ትመጣለች፤ ወደ ፍቅር ትመለሳለች፤ ቂምና በቀል ትጠፋለች ይላሉ አበው፡፡ ለምን ቢሉ ሽማግሌ በትሩን ይዞ የበደለ እንዲክስ፣ የተበደለ እንዲካስ እያደረገ መዋደድን ይዘራል፤ መለያየትን ጥሎ መቀራረብን ያበቅላልና፡፡ በሽምግልና ችግርን እየፈቱ መኖር በዚህች በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ የኖረ ነው፡፡

ታዲያ ሀገር ምድሩ ያከበራቸው ሽማግሌዎች፣ ሽማግሌ የሚቀመጥባቸው፣ ደም የደረቀባቸው ዋርካዎች፣ ለግዳይ በሚፈላለጉ ሰዎች መካከል ገብተው ግድያን የሚያስቀሩ ዘንጎች፣ ጠመንጃ እያዘለሉ በቀልን የሚሽሩ ብልህ አባቶች፣ ለዘመናት ፍቅር የጎመራባቸው የረቀቁ እና የተደነቁ እሴቶች ባልጠፉባት ሀገር ስለምን ፍቅር ቀነሰ? ስለ ምንስ ጥል ነገሠ?

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህሩ ብርሃን አሰፋ (ዶ.ር) ኢትዮጵያውያን በእሴቶቻቸው አማካኝነት ሥነ ምግባርን ሲያስተምሩ፣ ታሪክን ሲነግሩ፣ ሕግን ሲያስሩ፣ ሃይማኖትን ሲያጸኑ ኖረዋል ይላሉ፡፡ በእሴቶች አማካኝነት የትናንቱን ለዛሬ እየነገሩ፣ ለነገው ተስፋ እየሰጡ ይኖራሉ፡፡ እሴቶች ትናንትን ከዛሬ ጋር ያስታሳስራሉ፤ የቀደመውን ትውልድ ከዛሬው ጋር ያገናኛሉና፤ ለዚያም ነው ሀገር እንደጸናች፣ ከእነ ክብሯ እንድትቆይ የኾነች፡፡

አበው በእሴቶችቻው አማካኝነት መልካምነትን፣ ደግነትን፣ ሕግና ሥርዓትን እያስተማሩ፤ ክፉ ነገርን ደግሞ እያነወሩ ኖረዋል፡፡ ትውልድ ሁሉ ነውር እንዲያውቅ፣ ደግነትን እንዲወርስ፣ አንድነትን እንዲያነግሥ እያደረጉ መጥተዋል፡፡ አባቶች በእንስሳት ገጸ ባሕሪያት አማካኝነት እያዋዙ፣ እያዝናኑ ውስጠ ወይራ የኾነ ቁም ነገር ሲያስተምሩ ኖረዋል ይሏቸዋል፡፡ ለመጥፎዎች መጥፎ ተምሳሌትን፣ ለመልካሞቹም መልካም ተምሳሌትን እየሠጡ ትውልድን ቀርጸዋል፡፡

መልካምነትን፣ በጎነትን፣ አብሮ መኖርን፣ መተሳሰብን፣ ሰላምን፣ መረዳዳትን እየሰበኩ መጥተዋል፤ እነዚህን በመስበካቸው ደግሞ ሀገር በፍቅር አቆይተዋል፡፡

ሽማግሌዎችን ማክበር፣ ቃላቸውን መስማት የቆዬ እሴት ነው ይላሉ፡፡ በቀደመው ዘመን ሽማግሌ ወይም የሃይማኖት አባት ከገዘተ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚንቀሳቀስ አልነበረም፡፡ ግዝት እንኳን ሰው ወንዝ ያቆማል ተብሎ ይታመናልና፡፡

እኒያ ሀገር ያቆሙት፣ ትውልድ የቀረጹት፣ ሰላምን ያጸኑት እና አንድነትን ያበረቱት እሴቶች አሁን ላይ እንደተራ ነገር መቆጠራቸው አሁን ላለው ሰላም እጦት፣ አለመረጋጋት ዳርጓልም ነው የሚሉት፡፡ እሴቶችን አጥብቆ መያዝ የሀገርን ሰላምን መጠበቅ ነውም ይላሉ፡፡

ሀገረ ሰባዊ ሽምግልናዎች በሐቅ ላይ የተመሠረቱ፣ እውነትና እውነትን ብቻ ይዘው የሚነሱ፣ ሽማግሌዎችም ለማስታረቅ ሲነሱ በነፍሳቸውም በስጋቸውም ቃል ኪዳን ገብተው፣ በሐሰትም ቢመሰክሩ፣ በሐሰትም ቢፈርዱ የበደል ዋጋ እንቀበላለን እና እያሉ ፈጣሪያቸውን እያሰቡ ይገባሉ ነው የሚሉት፡፡

ሽማግሌዎች በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የሚታመንባቸው፣ እውነትን እንጂ ሐሰትን የማያደርጉ ናቸው፤ እውነትን እና እውነተኛ እርቅን የሚፈልጉ ሁሉ ወደ ሽማግሌዎች ይሄዳሉ ይሏቸዋል፡፡

ባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች አንደኛውን አሥረው አንደኛውን ነጻ የሚለቁ አይደሉም፡፡ ፍርድ ሳያጓድሉ ነገር ግን ሁለቱም በሚስማሙበት እና ለወደፊት ፍቅር በሚገበዩበት መንገድ ያስታርቃሉ እንጂ፡፡ የሽማግሌዎች ፍርድ ተፈጻሚነት ያለው ታራቂዎቹ ወደውት፣ አምነውበት እና አክብረውት የሚፈጽሙት ነው፡፡ አሁን ግን ይላሉ የባሕል ጥናት መምህሩ እውነትን ሳይኾን ጥቅምን መሠረት ያደርጋል፤ በሐቁ እና በእውነታው መዳኘት፣ እርቅም ማውረድ ሲያቅተው ሀገረሰባዊ ሽምግልናዎችን ይተዋቸዋል፣ ሽማግሌዎችንም ክብር ይነፍጋቸዋል ይላሉ፡፡

በሽምግልና እንደሚፈረድበት የሚያውቅ ሽምግልናን ይተዋል ነው የሚሉት፡፡ በኢትዮጵያ ባሕል እና እሴት ውስጥ የሽማግሌን ቃል ያላከበረ፣ ውሳኔውን የጣሰ ማኅበራዊ እገዳ ይጣልበታል፤ ከማኅበራዊ እገዳ የሚያመልጥ የለም፤ ከማኅበራዊ እገዳ ለመውጣት የፈለገ ሁሉ የሽማግሌዎች ቃል ያከብራልም ይላሉ መምህሩ፡፡

አሁን አሁን አልፎ አልፎ ፖለቲከኞች በሀገረ ሰበዓዊ ሽምግልናዎች የሚፈጸሙትን እርቆች ማፍረስ ወይም በእነርሱ ላይ ያለውን እምነት መተው ሲመጣ ለዘመናት ሀገር የጸናባቸው እና አንድነት የጠበቀባቸው እሴቶች  እንዲተዉ እያደረጋቸው መኾኑንም ያነሳሉ፡፡

እያወቁም ኾነ ሳያውቁ ሀገረሰበዓዊ ሽምግልናዎችን ክብራቸውን እየጣሱ እና እየናቁ መምጣት የግጭት መፍቻ ተቋማቱ እምነት እንዲታጣባቸው፣ እንዳይከበሩ እያደረጋቸው ነውም ይላሉ፡፡ ማኅበረሰቡ ሀገረሰባዊ ሽምግልናዎችን ያከብራል፤ አድርግ የተባለውንም ያደርጋል። በቀጣይም ይህ የእርቅ መፍቻ መንገድ ውጤታማ እንዲኾን ፖለቲከኞችም ተገዢ ሊኾኑበት ይገባል። ይህ ሳይኾን ሲቀር እና ሽምግልና በተጽዕኖ ሲኖር ከክብሩ እና ከዓላማው ይዘናፋል ነው የሚሉት፡፡ ሽምግልና ሚዛን ነውና በሚዛኑ ብቻ መኖር የተገባ ነው፡፡ ሽማግሌዎችን አንድ ወገን ብቻ የእኔን ሃሳብ አራምድልኝ፣ የእኔን ሃሳብም አስፈጽምልኝ፤ እንዲያ ካልኾነ አትቀረበኝ ከተባለ አካሄዱ እንደሚዛባም ያነሳሉ፡፡

የጥንቱን የሽምግልና ሥርዓት መጠቀም በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ይፈተዋልም ይላሉ፡፡ ሽምግልናን ማክብር እና በሽምግልና ውሳኔ መጽናት ቢቻል አሁን ላይ ያለው ችግር አይኖርም ነው የሚሉት፡፡ ሽማግሌዎች አሁን ያለውን ችግር የመፍታት አቅም አላቸው፤ ዋናው ጉዳይ ግን ማን ይሰማቸዋል? የሚለው ጥያቄ  ነው ይላሉ፡፡ ተናጋሪ እያለ ሰሚ ሲጠፋ አካሄዱም የከፋ ይሆናል፡፡ ሰሚ በታጣ ጊዜ ደግሞ እውነትን የሚናገሩ አንደበቶች ዝም ይላሉ፡፡ ዝም ማለት ሲመጣ ደግሞ ሀገር ትናጋለች፣ በአመጽ ትጨነቃለች፡፡

በኢትዮጵያ ከዓመታት ወዲህ የመጣው እና ከኢትዮጵያዊ እሴት የወጣ ባሕሪ የሃይማኖት አባቶችን ዝቅ ከማድረግ ጀምሮ የሃይማኖት ተቋማቸውን  እስከማፍረስ ተደርሷል። መተሳሰብ እንደቀድሞው ሲቀር አንድነት እንዲላለ ኾነ፤ በቀደመው ዘመንማ የሃይማኖት አባትን መሰደብ እና መግደል ይቅርና ፊት ለፊታቸው ለመቆም ያስቸግር ነበር ነው የሚሉት መምህሩ፡፡

ሽማግሌ ሲያልፍ ከተቀመጡበት ተነስቶ እጅ መንሳትን፣ ሮጦ ሄዶ ጉልበት መሳምን፣ ታዝዞ መመረቅን ሳይኾን ሽማግሌን ማዋረድ፣ መስደብን፣ መናቅን እየተለማመድን መጣን፤ መጥፎነትን፣  አለመከባበርን ለመድን፤ ይሄ ደግሞ ለችግር አጋለጥን ነው የሚሉት፡፡

ለኢትዮጵያውያን የሚሆነው፤ ከሥነ ልቦናቸው ጋር የሚስማማው ኢትዮጵያዊ የኾነ ሕግና ሥርዓት ነው ይላሉ፡፡ ከውጭ የተቀዳ ሕግና ሥርዓት ኢትዮጵያውያንን የራሳቸውን ያሳጣቸው ካልኾነ በስተቀር ችግሮቻቸውን አልፈታላቸውም፤ ይሄን ደግሞ ለዓመታት አይተነዋል፤ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያውያን የሚጠቅመውን እሴት መቅዳት፣ የተውጣጣውን መልካም እሴት አንድ ወጥ የሆነ ሕግና ሥርዓት ማድረግ ይገባል ነው የሚሉት፡፡

ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አውጣጥተው የሚያረቅቁት ሕግ እና ሥርዓት ችግራቸውን ያውቃል፤ ሥነ ልቦናቸውንም ያከብራል ይላሉ፡፡ ከውጭ እንኳን መቅዳት ካስፈለገ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን እንዲስማማ ኾኖ መቀዳት ይገባዋል ነው የሚሉት፡፡

የጸና ሰላም እንዲኖር ከተፈለገ ባሕላዊ እሴቶችን አጥብቆ መያዝ፣ እሴቶችን ለትውልድ ማስተማር፣ ከውጭ ይልቅ ራስን መመልከት፣ ለዘመናት ያቆመን ነገር ምንድን ነው? ብሎ ወደኋላ መለስ ብሎ መፈተሸ  ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡ እሴቶችን መያዝ ካልቻልን እና በእሴቶች ችግሮችን መፍታት ካልተቻለ ግን መጠፋፋት ይመጣ ካልኾነ በስተቀር ወደ ፊት መራመድ አንችልም ይላሉ፡፡

ሰውን ማሸነፍ የሚቻለው ልቡን ማሸነፍ ሲቻል ነው የሚሉት የባሕል ጥናት መምህሩ እሴትን ማክበር፣ ታላላቆችን መስማት ከችግር ያወጣል ነው የሚሉት፡፡ ታላላቆችን መስማት ካልተቻለ ግን የከፋ ችግር ይገጥማል፡፡ መጨረሻው እርቅ መኾኑ ላይቀር ብዙ ሰዎችን ማጣት አይገባም፤ ልብን ገዝቶ ችግሮችን መፍታት ይገባልም ይላሉ።

ግጭት ሌላ ቂም እና በቀል እየፈጠረ ይሄዳል፤ ሰላም ግን በቀልን ይገድላል፤  በጦርነት የሚፈታ ችግር የለም፤ ይህ የዓለም ልምድም አይደለም፤ የእኛ ታሪክም አይደለም፤ ሰላም የሚመጣው በሰላም ነው፣ የሕዝብን ሥነ ልቦና መረዳት ይገባል ይላሉ፡፡ ሀገር የጸናችው በእርቅ መኾኑንም ያነሳሉ፡፡ 

ማን ይኾን እንደ አባቶቹ የሚኾነው? ማንስ ይኾን የአባቶቹን ቃል የሚሰማው? በጎ ምክርን የሰማ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠበቃል፤ ከጥልና ከጥላቻ ይርቃልና፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን አቅሞች በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመረውን ውጤታማ የአመራርነት ሚና አጠናክሮ ይቀጥላል” አቶ አደም ፋራህ
Next articleየበላይነህ ክንዴ ፍውንዴሽን እና ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሠነ የግል ድርጅት በጋራ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ።