የበላይነህ ክንዴ ፍውንዴሽን እና ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሠነ የግል ድርጅት በጋራ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ።

74

ደብረ ብርሃን: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሁለቱ ተቋማት በጋራ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 375 ኩንታል የዳቦ ዱቄት በመጠለያ ጣቢያው ለሚገኙ ወገኖች አስረክበዋል።

የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው እንደተናገሩት ዱቄቱን ለመግዛት ድርጅታቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሲለግስ ወረታ ኢንተርናሽናል 5 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል። ድርጅታቸው የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በማንነታቸው ምክንያት ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ችግር ውስጥ ባሉበት በዚህ ጊዜ ድርጅቶቹ ላደረጉት ሰብዓዊነት ለተሞላበት ተግባር የከተማ አሥተዳደሩ ምሥጋናውን አቅርቧል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማዋ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ሩቅያ አሕመድ እና አቶ ይርጋ ዘገየ ህፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ብለዋል። በተለይም የምግብ እጥረቱ ከፍተኛ ስለኾነ ሁሉም ሰው ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ዘጋቢ: ብርቱካን ማሞ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጎ ምክር የሰማ ይሻገራል፣ ምክርም ያልሰማ ይወድቃል”
Next article“ተምረን ጥሩ ውጤት ማምጣት፣ ተወዳድረን ማሸነፍ እንጅ እየተተኮሰብን ወደኋላ መቅረትን አንሻም” ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች