
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን አቅሞች በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመረውን ውጤታማ የአመራርነት ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የኾነውን የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ትናንት መርቀው ከፍተዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ኢትዮጵያ ብዙ አቅም ቢኖራትም ወደ ልማት መለወጥ ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም በየአከባቢው ያሉ አቅሞችን በአግባቡ አይቶ፣ አቅሞችን ወደ ተጨባጭ ሀብት በመቀየር የሕዝብን ተጠቃሚነት ከማረጋግጥ አኳያ የአመራር ውስንነት ዋነኛው ምክንያት መኾኑን አንስተዋል።
በተለይም የመሪዎች የሃሳብ አመንጪነት እንዲሁም የማስፈጸም አቅም አናሳ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመፈጠሩን ተከትሎ በሚነሱ ግጭቶች የሚመጣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ጸጋዎችን ለመጠቀም አዳጋች እንደነበር አንስተዋል።
የብልጽግና ፓርቲም በሀገሪቱ በተለያዩ ሥፍራዎች ያሉ አቅሞችን አሟጦ ለመጠቀም አመራሩ ሚናውን እንዲወጣ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሃሳብ አመንጪነት ትናንት የተመረቀው የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ሀገሪቱ ያሏትን እምቅ አቅሞች እንድትጠቀም በተለይም በሀገራዊ ምክክሩ አማካኝነት ልዩነቶች እንዲፈቱ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የሃሳብ ኃይል ምን ያክል ወሳኝ እንደኾነ ትምህርት የሚወሰድባቸው መኾናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ትልቅ ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲሁም በከፍተኛ የጥራት ደረጃ እንዴት ማጠናቀቅ እንደሚቻል የፕሮጀክት አመራር ጥበብን የተማርንባቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ መኾናቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ሕዝቡን በሁሉም ደረጃ በማሳተፍ የሕዝቡን ተጠቃሚነትና የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ የታያዙ ውጥኖች እውን እንዲኾኑ ይሠራል ብለዋል።
በመኾኑም በቀጣይም የብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን አቅሞች በመጠቀም ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመራቸውን ውጤታማ የአመራርነት ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!