”ታላላቅ ኢንዱስትሪዎችን ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ነን” የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ

36

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ከ3 ሺህ 470 በላይ ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ እና ተጨማሪ ኢንዱስትሪዎችም እየተገነቡ መኾኑን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ ታረቀኝ ተናግረዋል።

”አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ዘርፉ እንዲመጡ እና የነባሮቹን የማምረት አቅም ለማሳደግ የግብዓት፣ የገንዘብ እና የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ጠንካራ ሥራ እየሠራ ይገኛል” ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው።

ኀላፊው በ2015 ዓ.ም 255 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ገብተዋል ብለዋል። በ2016 ዓ.ም ማሽን በማስገባት እና በሙከራ ምርት ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

”ታላላቅ ኢንዱስትሪዎችን ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ነን” ያሉት አቶ ተፈሪ ከተከላ እስከ ሙከራ ደረጃ ከሚገኙት ኢንዱስትሪዎች ውስጥም የመኪና መገጣጠሚያ፣ የምግብ ምርት ማቀነባበሪያዎች፣ የጣውላ እንዲሁም የብርጭቆ እና መስታዎት ፋብሪካዎችን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለው የሰላም ችግር በዘርፉ ላይ ጫና ማሳደሩን የጠቀሱት አቶ ተፈሪ ”የሰላም ችግሩም ራሳችን የሚጎዳ አቅማችን የሚቀማ ነው” ብለዋል። ”ግብዓቶችን ወደ ፋብሪካ፤ ምርትን ወደ ገበያ ለማድረስ የሰላም ችግሩ ጫና አሳድሯል” ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ተፈሪ ካልተመረተ የገበያውን ፍላጎት ማሟላት አይቻልም፤ ገበያ ላይ ምርት ከሌለ የኑሮ ውድነት ይፈጠራል፤ ባለሀብትም ገንዘቡን አፍስሶ ለማምረት ሰላም ይፈልጋል ሲሉ ጠቅሰዋል። የሰላም እጦትን እና የኑሮ ውድነትን ትስስር ያመላከቱት አቶ ተፈሪ ሁሉም ሰው የሰላም ችግሩ እንዲስተካከል ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

ዩኒሰን የምግብ ዘይት ፋብሪካን የጎበኙት አቶ መከተ ፈቃዴ እና አቶ ዘላለም እውነቱ ጉብኝታቸው ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ለማጠናከር እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። የተፈጠረ ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም በኩል የመንግሥት ሠራተኛው ምን ሚና እንዳለው አውቆ በቁርጠኝነት ለመሥራት ጉብኝቱ ጠቃሚ እንደኾነ ተናግረዋል።

የተከሰተው ግጭት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ጫና ማሳደሩን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ ክልሉ ያለበትን የሥራ እንቅስቃሴ እና የምጣኔ ሀብት እጥረት ለመቅረፍ ኅብረተሰቡ በመተባበር እና አስተሳሰብን በማሳደግ መሥራት እንደሚገባው ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጥር ወር የተጫዋቾች ዝውውር በርካታ ክለቦች ፉክክር ወስጥ ገብተዋል።
Next article“ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን አቅሞች በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመረውን ውጤታማ የአመራርነት ሚና አጠናክሮ ይቀጥላል” አቶ አደም ፋራህ