
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ፖርቱጋላዊውን የተከላካይ አማካኝ ተጫዋች ጆአዎ ፓልሂንሃ በ60 ሚሊዮን ዩሮ ለማዛወር እየተንቀሳሰ መኾኑ እየተዘገበ ነው፡፡
ሊቨርፑል እና አርሰናልም በ28 ዓመቱ አማካይ ጆአዎ ላይ ዓይናቸውን እንደጣሉበት ቢቢሲ ጨምሮ ዘግቧል፡፡
አርሰናል የ27 ዓመቱን እንግሊዛዊ የፊት መስመር ተጫዋች ኢቫን ቶኒን ለማስፈረም ለብሬንትፎርድ ጥያቄ ለማቅረብ እየተዘጋጀ መኾኑ ተሰምቷል፡፡
የፈረንሳዩ ስመ ጥር ክለብ ፒኤስጂ ሉካስ ቤራልዶን በ17 ሚሊዮን ፓወንድ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሷል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
የ20 ዓመቱ ብራዚላዊ የመሐል ተከላካይ በጥር ወር ሳኦ ፓወሎን መልቀቁ “እርግጥ ነው” ተብሏል፡፡
የጣልያኑ ኢንተር ሚላን በጥር የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት የ24 ዓመቱ ካናዳዊ የፊት መስመር ተጫዋች ታጆ ቡቻናን ለማስፈረም ጫፍ ደርሷል፡፡
ተጫዋቹ ከቤልጂየሙ ኀያል ክለብ “ብሩጅ” ጋር ያለውን ስምምነት ሊያጠናቅቅ መቃረቡንም ዴሎ ስፖርት ዘግቧል። ታጆን በጥር የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ ወደ ኢንተር ሚላን ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል።
አስቶንቪላ እና ቶተንሃም የ20 ዓመቱን የጁቬንቱስ የክንፍ መስመር ተጫዋች ሳሙኤል ኢሊንግ-ጁኒየርን በ17 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ፉክክር ውስጥ ገብተዋል፡፡
ለተጫዋቹ የተሻለ ጥቅም የሚያቀርብ ክለብ ያስፈርመዋል እየተባለ ነው፡፡
ዌስትሃም ከቡንደስ ሊጋ ይልቅ ወደ ፕሪምየር ሊግ መዛወርን የሚመርጠው የ27 ዓመቱን ጀርመናዊ ተከላካይ ጆናታን ታህን ለማስፈረም ከጀርመኑ ኀያል ክለብ ባየር ሙኒክ ጋር ፉክክር ውስጥ መግባቱን ቢልድ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!