“ሀገር የምትመስለው ዜጎቿን ነው፤ ዜጎችም የሚመስሉት የትምህርት ሥርዓቱን ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

16

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና ያስፈተኗቸውን ሁሉንም ተማሪዎች ላሳለፉ ትምህርት ቤቶች የዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እንዳሉት በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ 44 ወንድ እና 11 ሴት በድምሩ 54 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት አስመዝግበዋል። በማኅበራዊ ሳይንስ ደግሞ አምስት ወንድ እና አንድ ሴት በድምሩ ስድስት ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት አስመዝግበዋል።

በክልል ደረጃ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት 646 በተፈጥሮ ሳይንስ ከደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲኾን፣ በማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ደግሞ 533 ከክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተመዝግቧል።

ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስቲም ትምህርት ቤት ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ማሳለፋቸውን ቢሮ ኀላፊዋ ተናግረዋል።

ዶክተር ሙሉነሽ ፈተናው በሚሰጥበት ወቅት በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር እና ሌሎችም መሰናክሎች ሳይበግሯቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ክብር ይገባቸዋል ብለዋል። እነዚህ ተማሪዎች ለራሳቸው ብርቱዎች ናቸው፤ የነሱን ፈለግ ለሚከተሉ ተማሪዎችም አርዓያዎች ይኾናሉ ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ። የዛሬው ሽልማትም የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ዕውቅና ለመስጠት እና ሌሎች የክልሉ ተማሪዎችም በርትተው እንዲማሩ መልእክት ለማስተላለፍ ነው ብለዋል።

“ሀገር የምትመስለው ዜጎቿን ነው፤ ዜጎችም የሚመስሉት የትምህርት ሥርዓቱን ነው” ሲሉም ኃላፊዋ ተናግረዋል። ብቁ፣ ንቁ እና ብርቱ ትውልድ ለመፍጠር ጥራት ያለው እና አካታች የትምህርት ሥርዓት መተግበር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ይህንን ለማድረግም እየተሠራ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።

ዶክተር ሙሉነሽ በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የተረጋጋ የትምህርት ሥራ ለማከናወን ችግር ገጥሞ እንደነበር ተናግረዋል። በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን በተደረገው ጥረት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ ትምህርት ቤቶች ወደ መማር ማስተማር እየተመለሱ ስለመኾኑም ገልጸዋል።

ዶክተር ሙሉነሽ “መጭው ታሪካችን የሚወሰነው ለትምህርት እና ዕውቀት በምንሰጠው ትኩረት ነው” ብለዋል። ሰላም ያለውን ፋይዳ በውል በመረዳት ሁሉም የክልሉ አካባቢ ወደ ዘላቂ መረጋጋት እንዲመለስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ እና የትውልድ መሰረት የኾነው የትምህርት ሥራ በውጤታማነት መከናወን እንዲችልም መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የኮይሻ የኀይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ጎበኙ።
Next articleበጥር ወር የተጫዋቾች ዝውውር በርካታ ክለቦች ፉክክር ወስጥ ገብተዋል።