
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር እያካሄደ ነው። በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ዛሬ ለሚሸለሙ ተማሪዎችም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። “ከችግር በላይ ኾናችሁ በጽናት የቆማችሁ፣ የላቀ ውጤትም ያስመዘገባችሁ በመኾኑ ሽልማታችሁ ከቁስም በላይ ነው” ሲሉም ተሸላሚዎችን አመሥግነዋል።
የዛሬ ተሸላሚ ተማሪዎች በቀሪው የትምህርት ጉዟቸው ኢትዮጵያዊ አመለካከት ይዘው ለሕዝብ የሚበጅ ሥራን ለማከናወን የሚያስችል ዕውቀት እንዲይዙም አደራ ብለዋል። “ለክልላችን ብሎም ለሀገራችን ጠንካራ እና በዕውቀት የተገነባ ትውልድ እጅጉን ያስፈልጋል” ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም የላቀ ዕውቀት ይዘው እንዲወጡ ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ተማሪዎች ከተቋማት ይዘውት ከሚወጡት ጥሩ ውጤት በተጨማሪ መልካም ሥነ ምግባር፣ የሚሠራ እጅ እና ሕዝብን የሚያገለግል አስተሳሰብ ይዞ መውጣትም ያስፈልጋል ብለዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ትምህርት ሰላምን ይፈልጋል፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ተማሪዎች ጊዜያቸውን እና ዕድሜያቸውን በትምህርት ላይ እንዲያውሉ ማድረግ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ማኅበረሰብ ለሰላም የሚኾን ሀቀኛ እና ከልብ የመነጨ የሰላም አማራጭን እየተከተለ ለሰላም መሥራት አለበት ብለዋል።
ጤናማ ሀገር እና ሥርዓት የመገንባት ሂደት ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት ያሥፈልጋል፤ ይህንን ለማምጣት ደግሞ የትምህርት ሥርዓትን እና ተደራሽነቱን በየጊዜው መፈተሽ እና እያስተካከሉ መጓዝ ለነገ የማይባል ሥራ ነው ብለዋል ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!