“የሕዝብን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉና ዘላቂ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች በምክር ቤቱ እየተሠራ ነዉ” አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

13

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ የመልማት፣ የመልካም አሥተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎች በአግባቡ የሚደመጡበት እንዲኾን በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

አቶ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹት ምክር ቤቱ ሕግ ማውጣት፣ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ አካላት በሚሠሯቸው ሥራዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እና የሕዝብ ውክልና ሥራዎች አንኳር ተግባራቱ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ምክር ቤቱ በሕዝብ ተወካዮች የሚመሠረት እንደመኾኑ የሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ የሚደመጥበት እንዲኾን በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ወደ ታች ወርደው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን መከታተል፣ ድጋፍ መስጠትና የሕዝብ ጥያቄዎችን ወደ ምክር ቤት ማምጣት ይኖርባቸዋል ያሉት አቶ ታገሰ፤ ምክር ቤቱ አሁን ካለውም በላይ በክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ላይ ጠበቅ ያለ ተጠያቂነት እያረጋገጠ መሄድ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡

“የውክልና ሥራችን ላይ ብዙ መለወጥ አለበት፡፡ በመኾኑም ተመራጩ በተመረጠበት አካባቢ ቢሮ ኖሮት መራጩን በቅርበት የሚያደምጥበት፣ በየደረጃው ካሉ አስፈጻሚዎችና የምክር ቤት አባላት ጋር እየተነጋገሩ ወደ ምክር ቤት የሚመጡ ጉዳዮች ከሕዝብ የሚነሱበትን ኹኔታ መፍጠር ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በስድስተኛው ዙር ምርጫ ይህን ኹኔታ ለመተግበር ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ታገሰ፤ አስፈላጊው የአሠራር ሥርዓት ቀደም ብሎ ባለመዘርጋቱ በታሰበው ልክ ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም ነው ያሉት፡፡

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ይህን ጉዳይ አጠናክሮ መተግበር እንደሚገባ የሚያመላክቱ በመኾናቸው በቀጣዩ ዙር ይህን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለማሻሻል ጥናት ተደርጎ ለትግበራ የሚያግዙ ሰነዶች መዘጋጀታቸውንም አመላክተዋል አፈ ጉባኤው። ከእነዚህ ሰነዶች አንዱ ሕግ በምክር ቤቱ ቀርቦ ከመጽደቁ በፊት ያለፈበትን ሂደት ለመገምገም የሚያስችል ነው፤ ይህም ከሌሎች ሕጎችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የተናበበ ዘመን ተሻጋሪ ሕግ ለማውጣት ያግዛል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን የሚያከናውንበት የቁጥጥርና ክትትል ማንዋል መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ቋሚ ኮሚቴዎች የየዘርፉን ሥራዎች በተቀመጠው ማንዋል መሠረት ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርጉ ያስችላል፤ ይህም በአላስፈላጊ ነገሮች የሚባክኑ ጊዜያትን በማስቀረት የሕዝብን ጥያቄ የሚመልሱና ለውጥ የሚያመጡ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በጥቅሉ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ማውጣት፣ የቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም የሕዝብ ውክልና ሥራዎች የሕዝብን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉና ዘላቂ ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አፈ ጉባኤው ጨምረው መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በወቅታዊ ጉዳይ ያስተላለፉት መልእክት፦
Next articleጫና የማይበግራቸው ባለምጡቅ አዕምሮዎቹ ሊሸለሙ ነው።