የወልድያ ከተማ ተለዋጭ መንገድ ፕሮጀክት ዋና ዋና የግንባታ ሥራዎች በተያዘው በጀት ዓመት ይጠናቀቃል ተባለ።

24

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በወልዲያ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን መንገድ የፕሮጀክት ዋና ዋና ሥራዎች በዚህ ዓመት መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን ተነግራል።

እስካሁን ያለው የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 58 በመቶ ደርሷል ተብሏል፡፡ ለመንገድ ግንባታዉ የተመደበዉ ከ1 ቢሊየን 207 ሚሊየን 407 ሺህ ብር በላይ ወጪ የሚሸፈነዉ በኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡

የመንገድ ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘዉ የኮምቦልቻ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ሲሆን የማማከር እና ቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ልደት እና ስማርት ኮንሰልቲንግ በጣማራ እያካሄዱት ይገኛሉ፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ መሃል ከተማውን በማቋረጥ እስከ ስቴዲየም ያለውን ዋና መስመር የሚሸፍን ይኾናል፡፡ የቀድሞ መንገድ ከሰባት ሜትር ያነሰ ስፋት የነበረው በመኾኑ እጅግ ጠባብ እና ለትራፊክ ፍሰትም አስቸጋሪ የኾነ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተገነባ የሚገኘዉ የመንገዱ የጎን ስፋት በዋናው መስመር 30 ሜትር እና ወደ ስታዲየም በሚወስደው በኩል ደግሞ 12 ሜትር ተጨማሪ ስፋት እንዲኖረዉ ተደርጎ እየተገነባ ነው፡፡ በተጨማሪም የእግረኛ እና የብስክሌተኞች መተላለፊያ እንዲሁም የአረንጓዴ ሥፍራ ግንባታን ያካተተ ነው።

በእስከ አሁኑ የግንባታ ሂደት የመሬት ጠረጋ፣ የሙሌት፣ የውኃ መፋሰሻ ቱቦ፣ የድልድይ ግንባታ እና መሰል የግንባታ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው። የአስፓልት ንጣፍ ሥራም እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በከተማዋ ውስጥ እንዲሁም መግቢያ እና መውጫ ላይ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡

ከዚህም ባለፈም በወልዲያ ከተማ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ የሚቀርፍ እና የከተማዋን ውበት የሚጨምር አንደሚኾን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የሰፈረ መረጃ ያሳያል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአጠቃላይ ግንባታው ሂደት 62 በመቶ ደርሷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚሠሩ የጎንደር ከተማ ሠልጣኞች ተናገሩ።