
አዲስ አበባ: ታኅሳስ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛዎቹ ክልሎች ላይ የተሳታፊ ልየታ ሥራውን እየሠራሁ ነው ብሏል። የሰራቸውን እና እየሰራቸው ያሉ ተግባራትን ለብዙኅን መገናኛ ተቋማት መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ቃልአቀባይ ጥበቡ ታደሰ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሰጠውን ኀላፊነት ለመወጣት ጠንክሮ እየሠራ ነው ብለዋል። ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰዓት አራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የመጀመሪያው ጉዳይ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፍጠር ነው ያሉት ቃል አቀባዩ የኮሚሽኑን የቤት ሥራ ሁሉም እኩል እንዲቀበለው ለማድረግ ከሁሉም የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም የሚዲያ ፎረም እንዲቋቋም ከማድረግ ባለፈ የኮሚሽኑን ውስጣዊ የኮሙኒኬሽን አቅም ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው። ከተግባቦት እና ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ሁሉም ማኅበረሰብ እንዲገነዘበው ለማድረግ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የገጽ ለገጽ ተግባቦት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በትላልቅ አደባባዮች እና ከተሞችም የማስታወቂያ ቦርዶችን በመስቀል ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሠራ እንደኾነ ተገልጿል። ከምሁራን፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራት እና ከተለያዩ የማኅበረሰብ መሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ ማኅበረሰቡ ስለ ምክክሩ ግንዛቤውን ከፍ ለማድረግ እየተሠራም ነው።
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ለመሥራት ጥረት ተደርጓል ያለው ኮሚሽኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን መነሻ ተደርጎ ተጀምሯል በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ይቀጥላል ብሏል።
ሁለተኛው የኮሚሽኑ ዋና ጉዳይ ተብሎ የተያዘው ከየወረዳው ተሳታፊ ግለሰቦችን መለየት ነው። በተመሳሳይ የአጀንዳ ልየታ ላይ ሃሳብ የሚሰጡ ተወካዮችም የመለየት ሥራ ጎን ለጎን እየተሠራ ነው።
በዚህም በሲዳማ፣ በቤንሻንጉል፣ በአዲስ አበባ እና በጋምቤላ ክልሎች ላይ በአብዛኛዎቹ ወረዳዎች ተሳታፊዎች ተለይተዋል። በአፋር እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ደግሞ ተሳታፊዎች ተለይተው የውክልና መረጣ ላይ ይገኛል ተብሏል።
ኮሚሽኑ እንደሀገር እስከ አሁን በ327 ወረዳዎች የአጀንዳ ሃሳብ የሚሰጡ ተወካዮች ተመርጠዋል። በተመሳሳይ በኦሮምያ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው። እነዚህ ክልሎች ላይ በአጠቃላይ ከ380 በላይ ወረዳዎች የተሳታፊ ልየታ ተሠርቷል።
ኾኖም አሁን ላይ ባለው ወቅታዊ ችግር በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መሠራት ያለበት ቅድመ ዝግጅት ቢደረግም የተሳታፊ ልየታም ኾነ የተወካዮች መረጣ አልተካሄደም። ከሁለቱ ክልሎች በስተቀር በሌሎች ክልሎች አብዛኛው ሥራ ተሠርቷል ነው የተባለው።
ሌላው በሦስተኛ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ከዲያስፖራ ማኅበረሰቡ ጋር ውይይቶችን ማድረግ ነው። ከዲያስፖራው ጋር መሥራት የተፈለገው ከማኅበረሰቡ ጋር ኮሚሽኑ የሚሠራውን ሥራ ማስገንዘብ እና እንዴት መሠራት አለበት የሚል ግብዓት ለማግኘት ነው ተብሏል። እስካሁንም በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ እና በአውሮፓ ምክክር ተደርጓል።
በአራተኛ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ያለው ደግሞ የአጀንዳ መሠብሠብ ሥራ ነው። በተለይም ምክክሩ ውጤታማ እንዲኾን በምን ላይ መነጋገር፣ መግባባት እና መወያየት አለብን የሚለው ዋና ጉዳይ ስለኾነ አጀንዳዎች መሠብሠብ ይኖርባቸዋል ተብሏል። አጀንዳ የሚሠበሠበው ደግሞ ከኅብረተሰቡ፣ ከተቋማት እና ጥናት ከሠሩ ግለሰቦች ነው።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ የራሱን ጥናት እያደረገ አጀንዳ እየሠበሠበ እንደሚገኝም አስታውቋል። ይህ የኮሚሽኑ ሥራዎች በሚፈለገው ልክ ተካሂዶ ውጤት እንዲያመጣም የሁሉም ማኅበረሰብ ተሳትፎ ከፍተኛ በመኾኑ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- አደራው ምንውዬለት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!