በሰሜን ሸዋና በደቡብ ወሎ ዞኖች የአፈር ማዳበሪያ የማቅረብ ሥራ ተጀመረ፡፡

21

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ ዞኖች ለቀጣዩ የመኸር ወቅት ጥቅም ላይ የሚውል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ የማቅረብ ሥራ መጀመሩን የየዞኖቹ ግብርና መምሪያዎች አስታውቀዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና የመምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ በ2016/17 የመኸር ወቅት ከ496 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ነው።

አርሶ አደሩ በመኸር ወቅት የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት እንዳይገጥመው ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ የአቅርቦት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በተለይም ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ባለፈው የመኸር ወቅት አጋጥሞ በነበረው እጥረት አርሶ አደሩ ለችግር ተዳርጎ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ መሰል ችግር እንዳይከሰት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከታቀደው ከ1 ሚሊዮን 6 ሺህ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ድረስ 222 ሺህ ኩንታሉ በዞኑ የማከማቻ መጋዘን ደርሷል።
ዘንድሮ ለማቅረብ የታቀደው የአፈር ማዳበሪያ ባለፈው ዓመት ከታቀደው ጋር ሲነጻጸር በ246 ሺህ ኩንታል ብልጫ አለው ብለዋል።

እየቀረበ ያለው የአፈር ማዳበሪያ በአራት የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች አማካኝነት እና በ287 መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለአርሶ አደሮች እዲሰራጭ ይደረጋል ብለዋል።

በዚህ ዓመት መንግሥት የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት ቀድሞ ሥራዎችን ማጠናቀቅ መቻሉን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር አለመኖሩን በመገንዘብ ከአጭበርባሪዎች እራሱን እንዲጠብቅም አሳስበዋል።

ከአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን በቀጣዩ የመኸር ወቅት የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በተደረገ ጥረት ከ122 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ማስገባት መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የገጠመው የማዳበሪያ እጥረት የመልካም አሥተዳደር ችግር ከመፍጠር ባለፈ በሰብል ልማት ላይም ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል። በተደጋጋሚ የተስተዋለው የማዳበሪያ እጥረት ዘንድሮ እንዳያጋጥም ማዳበሪያ ቀድሞ ወደ ዞኑ እየገባ መኾኑን ጠቅሰው፤ በዞኑ ለቀጣይ በልግ እና የመኸር እርሻ ጥቅም ላይ የሚውል ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እየገባ መኾኑን አስረድተዋል።

እስካሁን ድረስ 122 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ የገባ ሲኾን ከገባው ውስጥ ከ10 ሺህ የሚበልጠውን ወደ ወረዳዎች ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።ቀሪውን በቅርቡ በማስገባት በዞኑ የማዳበሪያ እጥረት እንዳይከሰት እንደሚሠሩም አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡ ማዳበሪያው ቀድሞ መግባቱ አርሶ አደሩ የግብርና ሥራውን ያለ ስጋት እንዲያከናውን ከማድረግ ባለፈ ምርታማነትን ለመጨመር ያግዛልም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የባሕር ዳር ከተማ ሰላም በልጆቿ ይጠበቃል፤ ነዋሪዎቿም ከቱሪዝም ጸጋዋ ተጠቃሚ ይሆናሉ” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት
Next articleበኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።