
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማን ሰላም የሚጠብቁ ሰላም አስከባሪ አባላት ሥልጠና ከዛሬ ታኅሳሥ 12/2016 ዓ.ም ጀምሮ መሰጠት ጀምሯል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኀላፊ ገበያው አዳነ ሥልጠናው ለሰላም አስከባሪ አባላት የዕውቀት፣ የክህሎት እና የግንዛቤ ትምህርት የሚሰጥበት ነው ብለዋል።
ኀላፊው እንዳሉት ሠልጣኝ ወጣቶች ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የከተማዋን እና የነዋሪዎቿን ሰላም ያስከብራሉ። ወጣቶች ተገቢውን ሥልጠና ወስደው በሰላም ማስከበር ሥራው ላይ መሳተፋቸው የተለያየ መልክ ያለውን ዝርፊያ ለመከላከልና የወንጀሉ ተሳታፊዎችንም እርምት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
ለወራት በዘለቀው የሰላም እጦት ችግር ምክንያት ለወትሮው ወደከተማዋ የሚመጡ የቱሪስቶች መጠን እንዲቀንስ ማድረጉ ይታወቃል። ይህም ነዋሪዎች ከከተማዋ የቱሪዝም ጸጋ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም አሳጥቶ መቆየቱም ይታወሳል።
ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች እና ሌሎችም አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት እንዲሁም ለተቋማቱ ግብዓት የሚያቀርቡ ነዋሪዎች በኢኮኖሚ ተጎድተው ቆይተዋል።
በከተማዋ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም በመሥፈኑ ጎብኝዎችን ተቀብላ በሰላም ማስተናገድ የምትችል ከተማ መኾኗም ተጠቁሟል። አሁን ላይ የሚሠለጥኑት የከተማዋ ሰላም አስከባሪ ወጣቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ደግሞ የከተማዋ ሰላም ሙሉ በሙሉ እንደሚረጋገጥ ተገልጿል።
“የባሕር ዳር ከተማ ሰላም በልጆቿ ይጠበቃል፤ ነዋሪዎቿም ከቱሪዝም ጸጋዋ ተጠቃሚ ይሆናሉ” ሲሉ ነው የተናገሩት አቶ ገበያው።
ሌሎች ወጣቶች እና መላው የከተማ ነዋሪዎች በየአካባቢው ከሰላም አስከባሪዎች ጋር በመቀናጀት ለከተማዋ ሰላም ተባባሪ እንዲኾኑም ጠይቀዋል።
ሥልጠናውን የሚወስዱ የከተማዋ ሰላም አስከባሪ አባላት ወጣቶችም የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የከተማዋ እና የአካባቢው ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ እና ያለሥጋት ሠርተው ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጠንክረው እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!