
ሰቆጣ: ታኅሳስ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ያጋጠመውን የሰላም እጦት ለመፍታት መንግሥት እና ሕዝቡ በጋራ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ለዚህም መንግሥት ከሕዝቡ የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የሰላም ጥሪ በማቅረብ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት እያሳየ ይገኛል።
ወጣት ግርማ ታከለ የጋዝጊብላ ወረዳ የአስ ከተማ ነዋሪ ነው። ሰላም ለፍጡራን ሁሉ አስፈላጊ ነው ያለው ወጣቱ ሰላም ከጠፋ ቀድሞ ተጎጁ አምራች የኾነው ወጣቱ ነው ብሏል፡፡
ለማይጠቅም ነገር ሕይዎትን ማጣት እንደማይገባም አስረድቷል፡፡ ወጣቱ የሰላም ጥሪውን ከልብ ወስዶ እና ያለውን ፋይዳ ተረድቶ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባም አስገንዝቧል።
ሌላዋ የጋዝጊብላ ወረዳ አስ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት ገነት ሲሳይም ጦርነት ለማንም አይጠቅምም ብላለች፡፡ “ያለንን የሃሳብ ልዩነት በሰከነ እና በተረጋጋ መንገድ በማቅረብ የክልሉንም ኾነ የአስ ከተማን ልማት ልናፋጥን ይገባል” ብላለች።
ወጣት አበበ መስፍን በበኩሉ “ሰላማችን በእኛ በወጣቶች እጅ ነው፤ ወጣቱ ወደ ቀልቡ ካልተመለሰ ሀገር ሰላም አትኾንም እና ለሰላም እንቁም” ብሏል።
ወጣቱ ከሚጎዱት ነገሮች እራሱን ማራቅ አለበት ያለው ወጣት አበበ ትክክለኛ መረጃ ከትክክለኛው የመገናኛ ብዙኅን በማድመጥ ለሰላሙ መረጋገጥ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርቧል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!