“በግጭቱ የሚሳካው የጠላት ግብ እንጂ የአማራን ሕዝብ ፍላጎት እንዳልኾነ አውቀን ሁላችንም ለሰላም መስፈን ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

17

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ሥራ አፈጻጸም ላይ ውይይት አድርጓል።

በወይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ሕዝቡ እየተንገላታ ነው ብለዋል።

እናቶች ህክምና እያገኙ አይደለም ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ በግጭቱ ምክንያት ክልሉ ከሌላው ክልል ጋር ሲነጻጸር ወደ ኋላ እንዲቀር ኾኗል ብለዋል።

“ከጦርነት፣ ከግጭት እና ከመገዳደል ያለንን ከማጣት ውጭ ሌላ ነገር አናተርፍም” ያሉት ኀላፊዋ ”ከጦርነት የሚያተርፉት መሣሪያ ሻጮች እና ዩቲዩበሮች ናቸው፤ ለዚያውም ሌላ ቦታ የሚኖሩ፤ እሱም ዘላቂ ትርፍ አይደለም” ብለዋል።

“በግጭቱ የሚሳካው የጠላት ግብ እንጂ የአማራን ሕዝብ ፍላጎት እንዳልኾነ ዐውቀን ሁላችንም ለሰላም መስፈን ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል” ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ለሕዝብ ሰላም መስፈን ሁሉንም መፍትሔዎችን መሞከር፣ መታገል እና አቅጣጫ መስጠት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ኀላፊዋ ያጣነውን በማሰብ መቆዘም ሳይኾን ያለንን እና የወደፊት ተስፋችንን በማሰብ መሥራት አለብን ነው ያሉት። ግጭት የሚያጋጥም ቢኾንም የሚፈታበትን መንገድ አስቦ የጎደለውን ለመሙላት እያንዳንዳችን ድርሻችን እንወጣ ሲሉም አሳስበዋል።

ሥራዎችን ስንገመግም መልካም ጅምሮችን በማበረታታት፤ እጥረቶችን ደግሞ ለማስተካከል በሚቻልበት መንገድ መወያየት ይገባል ነው ያሉት። የገጠመንን ችግር ለመፍታት ልጆቻችንን እና ወንድሞቻችንን መክረን ወደ ሰላም በማምጣት ለሰላም መስፈን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ425 ሺህ በላይ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር
Next articleወጣቱ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጋዝጊብላ ወረዳ የአስ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ፡፡