“ከ425 ሺህ በላይ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር

37

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱን በተዳጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ድርቅ በስፋት ከተከሰተባቸው አካባቢው መካከል ደግሞ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንደኛው ነው፡፡

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረስ የጸጥታ ሁኔታው ፈተና ሆኗል፡፡ ሁሉም ለሰላም ዘብ በመቆም በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን እንዲደግፍ ጥሪ መቅረቡንም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምህረት መላኩ በክረምት ወቅት በተፈጠረው የዝናብ እጥረት ድርቅ መከሰቱን ገልጸዋል፡፡ በሰዎች እና በእንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱንም ነው የተናገሩት፡፡

አቶ ምህረት “በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሰረት ከ425 ሺህ በላይ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። ከእነዚህ ወገኖች ውስጥ 180 ሺህ 580 ሺህ የሚሆኑት ለከፋ ችግር ተጋላጮች መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

የክልሉ መንግሥት፣ የፌዴራል መንግሥት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ሌሎች እንዲያውቁት ከተደረገ በኋላ በፌዴራል እና በክልል መንግሥት ቅንጅት የተሻለ ድጋፍ ለማድረግ መቻሉንም አመላክተዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እንቅፋት መሆኑንም አንስተዋል።

የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት የሚልኳቸውን ድጋፎች መንገድ ላይ እየተዘረፉ ስለመኾናቸውም አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ መኪኖች መዘግየትና የተከዜ ድልድይ መሰበር የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራውን አስቸጋሪ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የሰብዓዊ እርዳታ መዘግዬት በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ለከፍተኛ ጉዳት እንደሚዳርግም አመላክተዋል፡፡ የሰብዓዊ ድጋፉ እና ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ቁጥር እንደማይመጣጠንም ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ድጋፍ ያልደረሳቸው ወገኖች ስለመኖራቸውም ተናግረዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተከሰተው ድርቅ ከ10 ሺህ በላይ አንስሳት ሞተዋል፣170 ሺህ የሚኾኑት ደግሞ ተሰደዋል ነው የተባለው፡፡ የሰላም አማራጮችን በማጠናከር ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ሁሉም አካል ለሰላም በመሥራት ተጎጂዎችን መደገፍ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

ተከታታይነት ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ እና የእንስሳት መኖ ድጋፍ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ እስካሁን ድጋፍ ላደረጉት ሁሉ ምስጋና ያቀረቡት ኃላፊው በችግር ያሉ ወገኖች ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየታላቁ ሕዳሴ ግድብ ወቅታዊ መረጃዎች፦
Next article“በግጭቱ የሚሳካው የጠላት ግብ እንጂ የአማራን ሕዝብ ፍላጎት እንዳልኾነ አውቀን ሁላችንም ለሰላም መስፈን ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)