
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚመራው የልዑካን ቡድን በቼንዱ እያደረገ ባለው የሥራ ጉብኝት ላይ የባሕር ዳር እና ዱጃንየ ከተሞች ዛሬ የእህትማማችነት ስምምነት ተፈራርመዋል::
የባሕርዳር ከተማ ከንቲባ ጎሹ እንዳለማው እና የዱጃንየ ከተማ ከንቲባ ጃንያ ዳን ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን በቀጣይ ሁለቱ ከተሞች በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በፓርክ ልማት እና አስተዳደር እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት ስራዎች ዙሪያ አብሮ ለመሥራት ተስማምተዋል::
በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው የልዑካን ቡድን የቻይና የፓርክ ከተማ ተብላ በምትታወቀው ቼንዱ ከተማ የተለያዩ ፓርኮችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል::
በጉብኝቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው፣ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፣ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ፣ የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ጎሹ እንዳለማው፣ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ መኩሪያ መርሻዬ እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች መሳተፋቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል እና ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር በትብብር ለመሥራት የቻይና ከተሞች ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
ዘገባው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ነው ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!