የሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ ኑሯቸውን ለማሻሻል ወሳኝ ሚና እንዳለው የደሴ ከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡

25

ደሴ: ታኅሳሥ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና ሴፍትኔት ጽሕፈት ቤት ለአንደኛ ምዕራፍ የኑሮ ማሻሻያ ተጠቃሚዎች የሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ ለማስተላለፍ የምክክር መድረክ አድርጓል።

በምክክር መድረኩ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝን ጨምሮ ሌሎች የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች እና በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ ከ1ሺህ 440 በላይ የምግብ ዋስትና ተጠቃሚዎች ተገኝተዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች የሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ ኑሯቸውን በማሻሻል ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የሚደረግላቸውን ድጋፍ በዕቅድ በመጠቀም ለታሰበው ዓላማ ብቻ እንደሚያውሉም ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ኀላፊ ብርሃኑ ሙሴ በ2ኛ ዙር የሚደረገው የመሥሪያ ገንዘብ ድጋፍ ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡

የገንዘብ ድጋፉ የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ለኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከዚህ በፊት ከነበሩበት የኑሮ ደረጃ የተሻለ ገቢ ማመንጨት እንደሚያስችላቸው ነው ያብራሩት፡፡

በከተማዋ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ጉልበትን መሰረት አድርጎ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ላይ እንዲውል አሠራር መዘርጋቱንም አስገንዝበዋል፡፡

የዶሮ እርባታ፣ የጓሮ አትክልት እና መሰል ሥራዎች እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በዚህም ዓመትም ተጠናክረው እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የገንዘብ ድጋፉን በአግባቡ መጠቀም በሚቻልበት ሂደት ዙሪያ የግንዛቤ ፈጠራ ውይይትም ተካሂዷል፡፡

በቀጣይም ለተጠቃሚዎቹ የግንዛቤ ፈጠራ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡም ተገልጿል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የከተማዋ የሴፍትኔት ተጠቃሚዎች የተደረገላቸውን የገንዘብ ድጋፍ ለተፈለገው ዓላማ ብቻ እንዲያውሉ አሳስበዋል፡፡ በቀጣይም የከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ዘጋቢ።- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የትምህርት ሥራን ማስተጓጎል የትውልድ ክፍተትን የሚፈጥር የከፋ ድርጊት ነው” የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ
Next articleባሕር ዳር ከቻይናዋ ዱጃንየ ከተማ ጋር የእህትማማችነት ስምምነት ተፈራረሙ።