
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 11/2016 (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት ምክትል ቢሮ ኀላፊው አማረ ዓለሙ ተቋሙ የሥራ እድል እንዲፈጠር ማድረግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር እና የኢንዱስትሪዎችን ሰላም የማረጋገጥ ተልእኮ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አቶ አማረ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ተቋሙ መደበኛ ሥራውን ለማከናወን ከፍተኛ ጫና ፈጥሮበት እንደቆየ ገልጸዋል።
በሰላም እጦት ምክንያት በርካታ ኮሌጆች ሥራ አለመጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በምዕራብ አማራ የሚገኙ ኮሌጆች ችግር እንደገጠማቸው ነው የገለጹት፡፡
ምክትል ኀላፊው “የትምሕርት ሥራን ማስተጓጎል የትውልድ ክፍተትን የሚፈጥር ክፉ ድርጊት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በመኾኑም ለሕዝብ የሚያስብ ሁሉ ሰላምን በማጽናት ልጆች እንዲማሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ወላጆች፣ ተማሪዎች እና መላው ማኅበረሰብ ኮሌጆች እንዲጀምሩ መሥራት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል፡፡ በርካታ ኮሌጆች ለማስተማር ዝግጁ በመኾናቸው ወደ ኮሌጆች እየሄዱ ሥልጠናቸውን እንዲከታተሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ለዜጎች ሥልጠና አልተሰጠም ማለት የሥራ እድል አልተፈጠረም ማለት ነው” ያሉት አቶ አማረ የሥራ እድል መፍጠር ካልተቻለ ለክልሉ ሌላ ችግር እንደሚያመጣ አብራርተዋል። በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ የተያዘ ቢኾንም ከ110 ሺህ ለማይበልጡ ብቻ መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር አለመቻል በክልሉ የምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ለሥራ እና ሥልጠና ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች እና መምህራን ወደ ሥልጠና እንዳይገቡ መከልከል ተገቢነት እንደሌለውም ገልጸዋል፡፡ ሥልጠና እንዳይጀምሩ መቀስቀስ የክልሉን ነዋሪዎች የሚጎዳ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ምክትል ኀላፊው የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናን መውሰድ ለዜጎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡ ኮሌጆች ሳያሠለጥኑ ሲቀሩ ሊኖር የሚችለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ኪሳራ ግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል፡፡
ኮሌጆች ለተማሪዎቻቸው ጥሪ እያደረጉ ሥልጠናውን መስጠት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም ተማሪዎች እንዲሠለጥኑ ሰላም እንዲጠበቅ መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ ያለው የሰላም እጦት በክህሎት ግንባታው እና በሥራ እድል ፈጠራው ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ የተዘረፉ እና ውድመት የደረሰባቸው ተቋማት መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዘራፊው ማንም ይሁን የራስን ሃብት መዝረፍ ተገቢ አለመኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ለልጆቹ የሚተላለፉ ተቋማትን መጠበቅ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ ሀገራት እያደጉ ያሉት በቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠናዎች ላይ በመመርኮዝ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
በአማራ ክልል ወደ ኮሌጆች የሚመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሠልጠን የሚያስችል አቅም መኖሩንም አንስተዋል፡፡ በክልሉ በርካታ ኮሌጆች በመኖራቸው ተማሪዎች በፍላጎታቸው እንዲማሩ እና የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲኾኑም አቶ አማረ አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
