“ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ አረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች በጦርነት ጊዜ የሚደርስባቸውን ጉዳት በውል በመገንዘብ ለሰላም እንሥራ” የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ

44

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የበለጠ ተጎጂ እየኾኑ ካሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አዛውንቶች እና አካል ጉዳተኞች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ አካላት በግጭቱ ይበልጥ እንዳይጎዱ እና የሚያገኙት ግልጋሎት እንዳይቋረጥ እየሠራ መኾኑን የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገልጿል።

ቢሮው የ2016 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሟል። የቢሮው ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው የተፈጠረው የሰላም ችግር የበጀት ዓመቱን ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ለማካሄድ እንዳስቸገረ ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ዝና በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአረጋውያን ቤት ሥራ፣ የአቅመ ዳካሞች ድጋፍ እና ለተማሪዎች የደብተር ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል። ለዘርፉ የሚውል 19 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንም ተናግረዋል። ለተማሪዎችም 67 ሺህ ደርዘን ደብተር ተሰብስቦ ማከፋፈል ተችሏል ብለዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት በጸጥታ ችግርም ውስጥ ኾኖ ተቋማቸው የተለያዩ የማኅበራዊ ኹነቶችን በማክበር እና ግንዛቤ በመፍጠር የሕጻናት፣ አረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞችን ችግር የሚፈቱ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።

ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ጋርም በመተባበር ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፉ እንዲደርሳቸው መደረጉንም ወይዘሮ ዝና ገልጸዋል። ከዩኒሴፍ በተገኘ ድጋፍ 17 ሚሊዮን ብር ለችግረኞች እንዲሁም በዩ.ኤን.ዲ.ፒ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ሌሎች ድጋፎች መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል። የማደራጀት እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራም መሠራቱን ጠቅሰዋል።

”በሩብ ዓመቱ በችግርም ውስጥ ኾነን ሥራዎች እንዳይቆሙ ሠርተናል” ያሉት ምክትል ኀላፊዋ በቀጣይም ችግሮችን ተቋቁሞ ውጤት ለማምጣት ጥረት እንደሚደረግም አስገንዝበዋል።

ሥራ ተሠርቷል ቢባልም የሰላም ችግሩ የፈጠረው እንቅፋት ቀላል አለመኾኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ዝና አሁንም ችግሩ የወለዳቸውን አማራጮች ተጠቅሞ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስረድተዋል። “ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ አረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች በጦርነት ጊዜ የሚደርስባቸውን ጉዳት በውል በመገንዘብ ለሰላም እንሥራ” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወደ ኮሌጆች ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተማሪዎች መካከል 27 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ሥልጠና እየወሰዱ ነው” የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ
Next article“የትምህርት ሥራን ማስተጓጎል የትውልድ ክፍተትን የሚፈጥር የከፋ ድርጊት ነው” የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ