“ወደ ኮሌጆች ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተማሪዎች መካከል 27 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ሥልጠና እየወሰዱ ነው” የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ

30

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት በሥራ እና ሥልጠና ሥራው ላይ ጫና መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ የትምርት እና ሥልጠና ዳይሬክተር ሚልክያስ ታቦር የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ዜጎችን የክህሎት ባለቤት በማድረግ የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል በርካታ ዜጎች መደበኛ እና አጫጭር ሥልጠናዎችን ሲወስዱ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በክልሉ የሠልጣኞች እና የማሠልጠኛ ኮሌጆች ቁጥር እየጨመረ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ከመንግሥት ባለፈ ባለሃብቶችም በዘርፉ እየሠሩ መኾማቸውንም ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል 24 የፖሊ ቴክኒክ፣ 102 የቴክኒክ እና ሙያ እና 110 የግል ኮሌጆች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በጤና ጥበቃ እና በግብርና ቢሮ ሥር የሚገኙ የማሠልጠኛ ኮሌጆች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡ ኮሌጆቹ ለዜጎች የክህሎት እና የቴክኒክ ሥልጠና በመስጠት የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚልቁ ሠልጣኞች በመደበኛ ሥልጠና መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡ የመደበኛ ሥልጠናዎች ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አምስት ድረስ እንደሚሰጡም ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል ባለሙያ የማፍራት ዓላማ ይዞ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ቢሮው በ2016 በጀት ዓመት 91 ሺህ 916 ተማሪዎች በመደበኛው ሥልጠና ይገባሉ ተብሎ መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡ እስከ ሕዳር 30/2016 ዓ.ም ወደ ኮሌጆች የመጡ 7 ሺህ 660 ተማሪዎች ብቻ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከእቅዱ አንጻር 8 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

69 ሺህ 202 ነባር ተማሪዎችን ለማስተማር እቅድ ተይዞ እንደነበር የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከነባሮቹ መካከል 37 ሺህ 67 ተማሪዎች ብቻ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በነባር እና በአዲስ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ከ161 ሺህ 121 ተማሪዎች መካከል ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙት 44 ሺህ 727 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ መግባት ከሚገባቸው ተማሪዎች መካከል 27 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ሥልጠና እየወሰዱ መኾናቸውም ተመላክቷል፡፡ ወደ ማሠልጠኛ ኮሌጆች ከገቡት ይልቅ ያልገቡት ይልቃሉ፡፡

በክልሉ ካሉት ኮሌጆች መካከል 75 የመንግሥት እና 53 የግል ኮሎጆች ብቻ ሥራ ላይ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ሌሎች ኮሌጆች ወደ ሥራ አለመግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡
የትኛውም ዜጋ ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እየገባ አጫጭር ሥልጠናዎችን መውሰድ እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡ ቢሮው የአጫጭር ሥልጠናዎችን እየሠጠ ቢኾንም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መቀነስ እንደታየበትም ተመላክቷል፡፡

ሥልጠናዎች ዜጎች ክህሎት እንዲኖራቸው እና ተወዳደሪ ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽን እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ሀብታሙ ይታየው ቢሮው ለኢንተርፕራይዞች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ መሰረቶች እና የሥራ እድል ፈጠራ አቅሞች መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ለሀገር ምጣኔ ሃብት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

በዓመቱ 29 ሺህ 982 ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ አቅደው 3 ሺህ 991 ኢንተርፕራይዞችን መደገፋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በዓመቱ 13 ሺህ 445 ኢንተርፕራይዞችን ከደረጃ ደረጃ ለማሸጋገር አቅደው 759 ኢንተርራይዞች ደረጃቸውን ማሸጋገራቸውንም አመላክተዋል፡፡ በደረጃ ሽግግሩም ዝቅተኛ አፈጻጸም መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡ በየኮሌጁ አሠልጣኞች መመደብ እና የተሻለ ሥልጠና መሥጠት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የተቋማት አቅም ግንባታ አግባብነት እና ጥራት ማረጋገጥ ዳይሬክተር ሙላው ልመንህ ቢሮው ለመንግሥት ኮሌጆች እና ሙያ እና ቴክኒኮች ኮሌጆች እንዲኹም ለግል ኮሌጆች የሥልጠና ፈቃድ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ የመንግሥትም የግል ተቋማት ሥልጠና ለመስጠት ፈቃድ ሊኖራቸውን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ፈቃድ ሳይኖራቸው ሥልጠና መስጠት እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በርቀት ሥልጠና መስጠት የተከለከለ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ሠልጣኞች ፈቃድ ካላቸው ኮሌጆች ብቻ መሠልጠን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡ ተቋማት ከተቆረጠው መግቢያ ነጥብ በታች መቀበል እንደማይገባቸውም ገልጸዋል፡፡

ከተፈቀደው በላይ ሠልጣኝ መያዝ ሕገ ወጥነት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በተለይም የግል ተቋማት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ተቋማት ሕጋዊ የሥልጠና ሰርቲፊኬት መስጠት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሩሲያ ግዙፍ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ግሩፕ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማምረት ሊጀምር ነው።
Next article“ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ አረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች በጦርነት ጊዜ የሚደርስባቸውን ጉዳት በውል በመገንዘብ ለሰላም እንሥራ” የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ