
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)17 ግዙፍ አምራች ኩባንያዎችን የያዘው የሩሲያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ መወሰኑን ገልጿል።
ከ10 ቢሊየን ሩፕል በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገበው እና 17 ግዙፍ የሩሲያ አምራች ኩባያዎችን ያቀፈው አግሮ ግሩፕ ኢንቨስት የተሰኘ የሩሲያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ማምረት ለመጀመር መወሰኑን ገልጿል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ የኢንቨስትመንት ግሩፑን ዳይሬክተር ካትኮቭ ዴኒስ እና የሥራ ባልደረቦቻቸውን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንቨስትመንት ግሩፑ የደረሰበት ውሳኔ ትክክለኛ እና ጊዜውን የዋጀ መኾኑን አንስተው ኮርፖሬሽኑ በተለይም ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ያዘጋጀውን የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ማበረታቻዎች፣ መንግሥት ዘርፉን ለማበረታታት ባለፉት ዓመታት ያዘጋጃቸውን አስቻይ ፖሊሲዎች እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ማበረታቻዎችን በዝርዝር ለተወካዮቹ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ኢንቨስትመንቱ እውን እንዲኾን ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የኢንቨስትመንት ግሩፑ ዳይሬክተር ካትኮቭ ዴኒስ ለተደረገላቸው አቀባበል እና ገለፃ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የቅድመ ኢንቨስትመንት ጥናቶችን እና መረጃዎችን እያጠናቀረ መኾኑንም አሳውቀዋል።
በነበረው ውይይት በሩሲያ የሚገኘውን ከፍተኛ የጨርቃጨርቅ ገበያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራች ኩባንያዎች መጠቀም እንዲችሉም ውይይት ተደርጓል።
የኢንቨስትመንት ግሩፑ ተቀማጭነቱን በሩሲያ ፌደሬሽን ኦሪዮል ግዛት አድርጎ 17 አምራች ኢንዱስትሪዎችን የያዘ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ግሩፕ ነው ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!