ኢትዮ ቴሌኮም የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ፋይናስ ገበያን አስተዋወቀ፡፡

19

አዲስ አበባ፡ ታኅሣሥ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም የቴክኖሎጂውን አቅም በመጠቀም የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ፣ ቀልጣፋ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የዲጂታል ፋይናስ ገበያን (Digital financial market place) እንደ መፍትሄ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ፍሬሕይዎት ታምሩ ገልጸዋል፡፡

የዲጂታል ፋይናስ አገልግሎት ገበያ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎታቸውን ለደንበኞቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ በአንድ አውድ በዲጂታል አማራጭ እንዲያቀርቡ የሚስችል መፍትሄ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

አሠራሩ ደንበኞች ካሉበት ኾነው የእጅ ስልካቸውን ብቻ ተጠቅመው የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ያሰችላቸዋል ብለዋል፡፡ አገልግሎቱ የደንበኞችን የብድር እንቅስቃሴ እና በወቅቱ የመመለስ ልምድን በማገናዘብ ያለምንም የንብረት መያዣ የብድር አገልግሎትን ለመስጠት የሚያሰችል እንደኾነም ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡ አሁን ላይ ባንኮች ይህን እንዲያውቁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ነው የሚገልጹት፡፡

አገልግሎቱን ለመጠቀምም ከአሀዱ፣ ከሲንቄ፣ ከእናት እና ከአዋሽ ባንኮች ጋር ውይይት ተጠናቆ ከብሔራዊ ባንክ በሚያገኙት ይሁንታ አገልግሎቱን በቅርቡ እንደሚጀምሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አስረድተዋል፡፡ በተያያዘ ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ ዲጂታል አክሲዮን የግዥ እና የመሸጫ አውድን ተግባራዊ መድረጉን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ፍሬሕይዎት ፍቃድ የተሰጣቸው የቢዝነስ ተቋማት የአክሲዮን ግዥ እና ሽያጭ ሂደታቸውን ዲጂታል የማድርግ እድል እንደሰጣቸውም ጠቁመዋል፡፡ ወጭ ቆጣቢ በኾነ መንገድ አክሲዮናቸውን ለማኅበረሰቡ በስፋት እና በቀላሉ ተደራሽ የሚያደርጉበት እድል ስለመመቻቸቱም ነው ያብራሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል ኪሮስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተጀመሩ የሰላም መንገዶችን ለማስቀጠል መሪዎች ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሠራን ነው” የጋዝጊቭላ ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች
Next articleሩሲያ ግዙፍ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ግሩፕ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማምረት ሊጀምር ነው።