“የተጀመሩ የሰላም መንገዶችን ለማስቀጠል መሪዎች ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሠራን ነው” የጋዝጊቭላ ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች

12

ሰቆጣ: ታኅሳሥ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በርካታ ኃይሎች ለሰላማዊ ውይይት እየቀረቡ ነው።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የጋዝጊቭላ ወረዳ አሥተዳዳሪ ገብሩ አስማረ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከ20 በላይ ግለሰቦች መመለሳቸውን ገልጸዋል።

አቶ ገብሩ አመራሩ፣ የወረዳው ማኅበረሰብ፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በመቀናጀት በተሠራ የሰላም መድረክ በርካታ ለውጦችን መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሀገር ችግር የሚፈታው በሰላማዊ ውይይት ነው ያሉት አቶ ገብሩ አሁንም መንግሥት ያቀረበው ሁለተኛ ዙር የሰላም ጥሪ ሳይጠናቀቅ ወደ ሰላም እንዲገቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጋዝጊቭላ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለሙ ደባሽ በበኩላቸው የወረዳ መሪዎች ከመረጣቸው ሕዝብ ጎን በመቆም ለወረዳው ሰላም መረጋገጥ የሠሩት ሥራ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የሥራ ኀላፊዎች ከማኅበረሰቡ ጋር የጀመሩትን የሰላም ውይይት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ለሰላም በራችን ክፍት ነው ያሉት ኀላፊዎቹ ከአሁን በፊት የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት እንደተፈታ ሁሉ አሁንም ልዩነቶችን በመወያየት ለመፍታት ዝግጁ ነን ሲሉ ለሰላም ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት በርካታ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ወድመዋል” የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ
Next articleኢትዮ ቴሌኮም የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ፋይናስ ገበያን አስተዋወቀ፡፡