“በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት በርካታ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ወድመዋል” የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ

16

ታኅሳሥ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ጋሻ ባይነስ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ቡድን መሪ ናቸው፡፡ በከተማዋና በዙሪያዋ በተከሰተው የሰላም እጦት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወድመዋል፡፡

ሕዝባዊ የኾኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሠራባቸው ስፍራዎችም ሳይቀሩ ከጥቅም ውጭ ኾነዋል፡፡ በመኾኑም በ2016 ዓ.ም ስፖርታዊ ኹነቶችን ለማከናወን ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

ቡድን መሪው አያይዘዘውም የከተማዋን ሰላም ለመመለስ ስፖርት ወሳኝ መኾኑን አስታውሰው፤ ምቹ ኹኔታዎች ባሉባቸው አካባቢዎች አሁንም ቢኾን ለታዳጊዎችን ሥልጠና ለመስጠት ሙከራ ላይ እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡

አቶ ተስፋየ ንጉሴ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የስፖርት ዘርፍ ቡድን መሪ ናቸው። “ከሐምሌ ወር ጀምሮ በዞኑ በአብዛኞቹ ወረዳዎች መረጋጋት ባለመኖሩ እና በርካታ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በመውደማቸው እንቅስቃሴ መሥራት አልቻልንም” ብለዋል፡፡ ይህም ኾኖ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም እየመጣ ባለባቸው ወረዳዎች በተመረጡ የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮችን ለማስጀመር እየሠራን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ማኅበራት ዕውቅናና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ሉሌ እንዳሉት ስፖርት በባህሪው ሰላምን ማምጣት አለበት፡፡ ለምሳሌ በሀገረ ግሪክ 1896 አካባቢ በሦስት የጎሳ መሪዎች አማካኝነት ከፍተኛ ግጭት ተከስቶ ሀገሪቱ ምስቅለቅል ውስጥ ገብታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ የእነዚህን ጎሳዎች ልዩነት ስፖርታዊ ውድድሮች ያስማማቸው እንደ ነበር ተናግረዋል፡፡ በግጭት ውስጥ ያሉት ጎሳዎች ስፖርትዊ ውድድር ሲኖር በተቀደሰ ስምምነት የአንዱ ጎሳ አባል ከሌላው ጎሳ ጋር እንዲገናኝ ብሎም ወደ ፈለገው ቦታ እንዲሄድ ይደረጋሉ፡፡ በተጨማሪም ስፖርታዊ ውድድሮች በሚደረጉባቸው ቀናት ጦርነት ማድረግ አይቻልም። ስለዚህ ስፖርት ሰላምን ለማምጣት ትልቅ ኃይል እንዳለው ከግሪክ እንረዳለን ብለዋል አቶ ሙሉጌታ።

እኛም ከግሪክ ታሪክ ተምረን ስፖርት ሰላማን እንዲሰብክ በማድረግ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ወረዳዎች እና ዞኖች በርካታ ሕዝብ አሳታፊ የሚኾንበት የታዳጊዎችን ብሎም የጤና ውድድሮች በማከናወን ሁሉም ለሰላም መስፈን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አቶ ጋሻው ተቀባ “በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት በርካታ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ወድመዋል” ብለዋል። ይህም በበርካታ አካባቢዎች መደረግ የነበረባቸውን ውድድሮች እንዲቋረጡ አድርጓል ነው ያሉት።ከወረዳ ወረዳ ተንቀሳቅሶ መፎካከርም አልተቻለም፤ በመኾኑም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩም ከፍተኛ ሃብት አጥተናል ብለዋል፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ውድድሮች እየተደረጉ መኾኑን አንስተዋል። ለአብነትም በሰሜን ጎንደር ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ አትሌቶችን ያሳተፈ ውድድር ተደርጓል ብለዋል። ኃላፊው አክለውም በ300 ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችን ያሳተፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እየተከናወነ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ የክለቦች ውድድር እንዲጀመር እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ቢሮው የ2015 ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ፣ የ2016 ዕቅድ ትውውቅ እና የአንደኛው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በባሕር ዳር ተካሂዷል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ26 ሺህ በላይ የከተማ ነዋሪዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባል ማድረግ ተችሏል” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር
Next article“የተጀመሩ የሰላም መንገዶችን ለማስቀጠል መሪዎች ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሠራን ነው” የጋዝጊቭላ ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች