
ደብረ ብርሃን: ታኅሳስ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የ2016 ዓ.ም የንቅናቄ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ነው።
መምሪያው በ2014 ዓ.ም ከነበረበት ዝቅተኛ አፈፃፀም ወደ ላቀ ደረጃ የተሸጋገረበት ዓመት እንደነበር የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን በመድረኩ ላይ ተናግረዋል።
አቶ ገስጥ በ2015 ዓ.ም ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል። የላቀ አፈፃፀም ካስመዘገቡ ከተሞች መካከል የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር አንዱ እንደኾነ አስረድተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ በቀለ ገብሬ መምሪያው በበጀት ዓመቱ ጠንካራ ሥራዎች ሥለመሥራቱ ተናግረዋል። በዚህም ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል። ለውጥ ከታየባቸው መስኮች መካከል ጤና መድኅን ትልቁን ድርሻ ይይዛል። መምሪያው የእቅዱን 88 በመቶ መፈፀም ችሏልም ብለዋል።
በ2016 ዓ.ም ከ5 ሺህ በላይ አዲስ የጤና መድኅን አባላትን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ስለመኾኑም አብራርተዋል። “ከ26 ሺህ በላይ የከተማ ነዋሪዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባል ማድረግ ተችሏል” ያሉት መምሪያ ኀላፊው ነባሮቹም እንዲያድሱ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ለዚህም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ንቅናቄ መድረክን በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ይገኛል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ብርቱካን ማሞ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!