
አዲስ አበባ: ታኅሳስ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ”ጤና ለሁሉ፤ ጊዜው የተግባር ነው” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ ሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋን ቀን እየተከበረ ነው።
ጤና ሚኒስቴር እና የዓለም ጤና ድርጅት “ጤና ለሁሉ፤ ጊዜው የተግባር ነው” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ ሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋን ቀን እያከበሩ ነው።
ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽ ለማድረግ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ምክንያት በሚከሰቱ ችግሮች ፈተና እየገጠመው እንደኾነ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።
ዜጎች በአቅራቢያቸው ተደራሽ፣ ቀልጣፋ እና ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ማድረስ የግድ መኾኑንም ገልጸዋል። የጤና ፋይናንስ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል ሚኒስትሯ።
ሕጻናት እና እናቶች ላይ ያለውን የጤና ፋይናንስ እና ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል። የጤና መሠረተ ልማት ላይ ብዙ ሥራ የተሠራ ቢኾንም አሁንም በተለይ በጤና ጣቢያ ላይ ሰፊ ሥራዎችን መሥራት ተገቢ ይኾናል ብለዋል።
በተደራሽነት እና በጥራት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በዲጂታል ዘርፉ ለማዘመን ብዙ ሥራ ተሠርቷል፣ አሁንም ቢኾን ተጨማሪ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ካሱ ከተማ የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም ጤና ድርጅት የያዘውን ዓለም አቀፍ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት እያገዘ ነው ብለዋል።
50 በመቶ የዓለም ሕዝብ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት በቂ የጤና ሽፋን እንደማያገኙ ተወካዩ ገልጸዋል። ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች መሠረት ያደረገ የጤና አገልግሎት ሽፍን እንዲሳካ በተለይም በግሉ ዘርፍ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት የዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ እንደሚያደርግ ዶክተር ካሱ ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍ ያለው አገልግሎት ተደራሽነትን ጨምሮ ቀልጣፋ እና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ድርጅቱ እንደሚያደርግም የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን እረገድ እያሳየች ያለችውን መሻሻል እና ያሉትን ክፍተቶች የሚያመለክት የጥናት ውጤትም ቀርቧል።
ከጤና ሚኒስቴር እና ከዓለም ጤና ድርጅት በተጨማሪ የሲቪክ ማኅበራት እና ሌሎች ድርጅቶች እለቱን በማስመልከት ዛሬ የደም ልገሳ መርሐግብር እንደሚኖርም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል መላኩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!