“ሁሉም አርሶ አደር የተፈጥሮ ማዳበሪያን በብዛትና በጥራት እንዲያመርት በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

8

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በርካታ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት ላይ ናቸው። ምርታማነትን ለማሳደግ በቁጭት እየሠሩ ከሚገኙ መካከል አርሶ አደር፣ ጸጋየ ፈንታሁን ተይጠቀሳሉ።

አርሶ አደር ጸጋየ ፈንታሁን ከአሚኮ ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ “በችግር ውስጥም ቢኾን ሀገር እንድትለማ መትጋቴን እቀጥላለሁ” በሚል ቁጭት ነው እየሠሩ የሚገኙት።

አርሶ አደር ጸጋየ ፈንታሁን በደቡብ ጎንደር ዞን የአንዳቤት ወረዳ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ ሁሌም ከመኝታቸው በነቁ ቁጥር የሚያስቡት ከቤተሰባቸው አልፈው ሀገርን እንዴት መመገብ እንዳለባቸው ነው፡፡ አርሶ አደር ጸጋየ ሁሌም በተንጣለለው መሬታቸው ላይ ለሚያዘምሩት አዝመራ ምርታማነት ነው አስበው የሚሠሩት፡፡

ለዚህ ደግሞ እሳቸውም ይሁኑ ቤተሳባቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ጥረት እያደረጉ ነው የሚገኙት፡፡ ደጉ አርሶ አደር ጸጋየ ምንም እንኳን ለሥራቸው ሳንካ የሚኾን የሰላም እጦት ቢገጥማቸውም “በችግር ውስጥም ቢኾን ሀገር እንድትበለጽግ መትጋቴን እቀጥላለሁ” ብለዋል፡፡ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በማዘጋጀትም የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

የባለፈው የምርት ዘመን የማዳበሪያ እጥረትን በማየታቸው ዘንድሮ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደኾነም ገልጸዋል። 15 ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ 12 ሜትር ኩብ ብስባሽ ከባዮ ሰለሪና ከቨርሚ ኮምፖስትም ማዳበሪያ እያዘጋጁ መኾናቸውንም አስረድተዋል።

“የግብርና ባለሙያዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት እንደ ቀድሞው እየተመላለሱ ባያስተምሩንም እየደወሉ ኮምፖስት እንድናዘጋጅ መወትወታቸው አልቀረም” ያሉት አቶ ጸጋየ ”ባለሙያዎቹ በየቀያችን ባይመጡም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከማዘጋጀት ወደኋላ አንልም” ብለዋል። ባለፈው የምርት ዘመን ያጋጠመው የማዳበሪያ እጥረት አርሶአደሩን የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጅ እንዳበረታታው ነው የተናገሩት።

በደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አስፋው ይልማ በዞኑ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እየተዘጋጀ መኾኑን ገልጸዋል።
በዞኑ እስካሁን፦

👉16 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ኮምፖስት ለማዘጋጀት ታቅዶ 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ማዘጋጀት ተችሏል፡፡

👉324 ሺህ ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት ለማዘጋጀት ታቅዶ 1 ሺህ 151 ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት ተዘጋጅቷል

👉22 ሺህ ሜትር ኩብ ባዮ ሰለሪ ኮምፖስት ታቅዶ 2 ሺህ ሜትር ኪዩብ መመረቱን ገልጸዋል።

ቡድን መሪው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትን ለመከታተል እና ለመደገፍ የጸጥታው ችግር እንቅፋት መኾኑን ነው የተናገሩት።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አጠቃ አይቼው በክልሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፦

👉 102 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ብስባሽ ለማዘጋጀት ታቅዶ 39 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ብስባሽ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል፡፡

👉 2 ሚሊዮን ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት ለማዘጋጀት ታቅዶ 52 ሺህ ቨርሚ ኮምፖስት ማዘጋጀት ተችሏል፡፡

👉 292 ሺህ ሜትር ኩብ ባዮሰለሪ ታቅዶ 28 ሺህ ባዮሰለሪ ኮምፖስት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

”ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት የተሻለ አፈጻጸም ነበራቸው” ያሉት ባለሙያው አሁን ላይ በጸጥታው ችግር ምክንያት በዞኖቹ ሥራውን ለማስተባበር ባለመቻሉ የክልሉን ክንውን ዝቅተኛ አድርጎታል ብለዋል።

”የፋብሪካ ማዳበሪያ ለብዙ ዓመታት በመጠቀማችን በአፈር ለምነት ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ እና እጥረቱ ባጋጠመ ጊዜም የሚፈጠረውን ሀገራዊ ችግር አይተነዋል” ያሉት አቶ አጠቃ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በበቂ መጠን እና በጥራት በማምረት ከሚያጋጥም ችግር መውጣት ይገባል ነው ያሉት።

አርሶአደሩ፣ ባለሙያዎች፣ አመራሩ እና የምርምር ተቋማትም ሁሉም አርሶ አደር የተፈጥሮ ማዳበሪያን በብዛትና በጥራት እንዲያመርት ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ አቶ አጠቃ ከንግግር ያለፈ ተግባራዊ ሥራም እንደሚያስፈልግ ነው ያሳሰቡት።

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ5 ሺህ በላይ ታጣቂዎች ሰላምን መርጠው ወደ ማዕከሎች ገብተዋል” መንገሻ ፈንታው ( ዶ.ር)
Next articleበወገራ ወረዳ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ታጣቂዎች ወደ መቀበያ ማዕከላት መግባታቸው ተገለጸ።