“ከ5 ሺህ በላይ ታጣቂዎች ሰላምን መርጠው ወደ ማዕከሎች ገብተዋል” መንገሻ ፈንታው ( ዶ.ር)

101

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም ለሰላም ጥሪው ሕዝቡ ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል። የሀገር ሰላም የሚረጋገጠው እያንዳንዱ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መኾኑን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ወደ ቀደመው ሰላም ለመመለስ መንግሥት ሰፊ ጥረት ማድረጉንም ተናግረዋል። በየአካባቢው ሰፋፊ መድረኮች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በተፈጠረው የሰላም ችግር አርሶ አደሮች በሙሉ አቅም ወደ ልማት እንዳይገቡ፣ ዜጎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ እና መሠረተ ልማቶች እንዲጎዱ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ከሕዝብ የተነሳውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ መንግሥት የሰላም ጥሪ ማቅረቡንም አስታውሰዋል። የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ወጣቶች ታጣቂዎችን በማግባባት እንዲገቡ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በተሠራው ሥራ በርካታ ታጣቂዎች ገብተዋል ብለዋል።

በአራቱም ቀጣናዎች 5 ሺህ 216 ታጣቂዎች ሰላምን በመምረጥ ወደ መቀበያ ማዕከላት ገብተዋል ነው ያሉት። ለሰላም ሲመጡ መከላከያ ሠራዊት ጥበቃ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። ቀጣይም በርካታ ታጣቂዎች እንደሚገቡ ይጠበቃል ነው ያሉት። የገቡት ታጣቂዎች አስፈላጊው ጥበቃ እና እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሆነ አብራርተዋል።

ታጣቂዎችን ወደ ሥልጠና ማዕከል ለማስገባት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ምሁራን ያሳዩት ተነሳሽነት የሚደነቅ መኾኑንም አንስተዋል። ለሰላም መስዋዕትነት እንከፍላለን በሚል መሥራታቸውንም ተናግረዋል።

የቀረበው የሰላም ጥሪ ምላሽ ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል። ክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲኖረው፣ አርሶ አደሮች እንዲያመርቱ፣ በምጣኔ ሀብት ተወዳዳሪ መኾን እንዲቻል ሁሉም ለሰላም ዋጋ እንዲከፍልም ጠይቀዋል።

ታጣቂዎች ጥሪውን በመቀበል ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እያደረግን ነው” የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር
Next article“ሁሉም አርሶ አደር የተፈጥሮ ማዳበሪያን በብዛትና በጥራት እንዲያመርት በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ