
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ታኅሳሥ 29 የቅዱስ ላሊበላ ልደት ጋር በኢትዮጵያ በልዩ ሁኔታ በዳግማዊት ኢየሩሳሌም ደብረ ሮሃ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀት ይከበራል።
በየዓመቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ የዕምነቱ ተከታዮችና የውጭ ሀገር ዜጎች ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም የተወለደበትን ታኅሳሥ 29 በዳግማዊት ኢየሩሳሌም ደብረ ሮሃ በምሥጋና ያከብራሉ።
የልደት በዓል በላሊበላ የዕምነቱ ተከታዮች ፅድቅን የሚያገኙበት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ልደትን ለማክበር የሚመጡ ዕንግዶችን በማስተናገድ፣ እግር በማጠብ በረከትን፣ የዕርስ በርስ ግንኙነት የሚያጠናክርበትና ማኅበራዊ ቁርኝትን የሚያገኝበት ልዩ በዓል ነው።
ታህሳስ 29 የሚከበረውን የልደት በዓልንም በልዩ ሁኔታ ለማክበር ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ከተማ አሥተዳደሩ አስታውቋል።
የልደት በዓል ሲከበር ትልቁ ግብ በርካታ የዕምነቱ ተከታዮች በቦታው ተገኝተው እንዲያከብሩት ከማድረግ ባለፈ በኮሮናና በጦርነት የተጎዳውን የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማጠናከር መኾኑን የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጀ ተናግረዋል።
እንግዶችን በወጉ ተቀብሎ አስተናግዶ፤ በሰላም የመመለስ ማኅበረሰቡ የቀደመ ባሕል ያለው በመኾኑም ተገልጿል። እንደተለመደው ዘንድሮም እንግዶችን እየጠበቀ በመኾኑ የዕምነቱ ተከታዮች፣ ኢትዮጵያውያን፣ የውጭ ሀገር ዜጎች ልደትን በላሊበላ ተገኝተው እንዲያከብሩ ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የዕምነቱ ተከታዮች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የልደት በዓልን በላሊበላ ተገኝተው እንደሚያከብሩ ከላሊበላ ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!