‹‹የኅብረተሰቡን ችግሮችን ለመፍታት በየተቋማቱ የሚካሄዱ ጥናቶች ከመደርደሪያቸው ወርደው ወደ ተግባር መለወጥ አለባቸው።›› የውይይቱ ተሳታፊዎች

250

‹‹የኅብረተሰቡን ችግሮችን ለመፍታት በየተቋማቱ የሚካሄዱ ጥናቶች ከመደርደሪያቸው ወርደው ወደ ተግባር መለወጥ አለባቸው።›› የውይይቱ ተሳታፊዎች

8ኛው የተፈጥሮ ሳይንስ የምሁራን ውይይት በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፤ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የተፈጥሮ ሳይንስ ምሁራን በየጊዜው የሚካሄዱ ጥናቶች ወደ ተግባር እንዲለወጡ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየመከሩ ነው። ‹‹ዘርፈ ብዙና የተቀናጀ ሳይንሳዊ ጥናት ለተሻለ ሕይወት›› በሚል ሐሳብ ነው ምሁራኑ እየመከሩ የሚገኙት፡፡

የምሁራን ምክክር መድረክ ላይ ለመሳተፍ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጡት አቶ ንጉሴ ደርቤ በመድረኩ ላይ ከቀረቡ ጥናቶች ልምድ መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹እኔ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታ ጥናት እና ምርምር ማድረግ እንዳለብኝ ከመድረኩ ተረድቼያለሁ፡፡ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም የተለያዩ ጥናቶችን በማጥናት የአካባቢውን ማኅበረሰብ እየደገፈ ይገኛል›› ብለዋል፡፡

ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ትምህርት ክፍል የመጡት ዶክተር የእልፍዋጋሽ አስማረ የምርምር ሥራ ሲካሄድ በጋራ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከተባበርን ጠንካራ እንሆናለን፤ ተሰባስበን ከተመካከርን ከአዕምሯችን ውስጥ ያለው ዕውቀት ይወጣል፡፡ ጥናት ሲካሄድ ብዙ ገንዘብ ይፈስስበታል፣ ብዙ ጉልበት እና አዕምሮ ይፈጃል፤ ይህ ሁሉ ሀብት ባክኖበት በየመደርደሪያው ተከምሮ እና ወዳድቆ ሲታይ በጣም ያሳዝናል፡፡ ስለዚህ አንድ አጥኚ ትክክለኛ እና የሀገርን ዜጋ ኑሮ በሚያሻሽል መልኩ ማጥናት ይጠበቅበታል›› ብለዋል ዶክተር የእልፍዋጋሽ። ማኅብረተሰቡን ለማገልገል በየተቋማቱ የሚካሄዱ ጥናቶች ከመደርደሪያ ወርደው ወደ ተግባር መግባት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ የተካሄደው መድረክ ዓላማው ከዚህ በፊት የተካሄዱት ጥናቶች የደረሱበትን ደርጃ መገምገም እና የተጠኑ ጥናቶች ወደ ኅብረተሰቡ እንዲወርዱ ማድረግ ነው ያሉት ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ኮሌጅ ድህረ ምረቃ ምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን ፀጋዬ ካሳ (ዶክተር) ናቸው፡፡ ‹‹የአሁኑ የምሁራን ምክክር ጥናቶችን የመለየት ሥራ ነው፡፡ ከየዩኒቨርሲቲው የተገኙ ምሁራን ሐባቸውን በማንሸራሸር የትኞቹ ጥናቶች የዕውቀት ማፍለቅ (ቤዚክ ሪሰርች) ናቸው? የትኞቹ የተግባር እና ችግር ፈቺ ጥናት (አፕላይድ ሪሰርች) ናቸው ብለን በመለየት ችግር ፈቺ የሆኑትን ወደ ሕዝብ አውርደን ሕዝብን እንዲያገለግሉ እናደርጋለን›› ብለዋል፡፡

በ8ኛው የምሁራን ምክክር ወደ ቴክኖሎጂ የሚያሸጋግሩ ጥናቶችን እንደሚመርጡ ዶክተር ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶክተር ፀጋየ ማብራሪያ በመድረኩ እንዲሳተፉ የተደረጉት ምሁራን ባቀረቡት ጥናት ተወዳድረው አሸናፊ ከሆኑ በኋላ ነው፡፡ አስካሁን የተካሄዱ ጥናቶች እና ምርምሮች ከሚፈስባቸው መዋዕለ ንዋይ፣ ጉልበት እና ጊዜ አንጻር ሲታዩ የማኅበረሰቡን ሕይወት በመለወጥ ረገድ አመርቂ እንዳልሆኑ አብመድ ታዝቧል፡፡ ዛሬ የጀመረው የምሁራኑ የምክክር መድረክ ነገ የካቲት 14/2012 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

Previous articleቻይና የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የሚያስችሉ 100 ሺህ ዳክዬዎችን አሰማራች፡፡
Next article38 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትና መቅደላን ከታች ጋይንት የሚያገናኘው የበሽሎ ድልድይ ተመረቀ።