
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገመግም እና የቀጣይ አቅጣጫ ላይ የሚመክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ክልላዊ የፀጥታ ሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። አሁን ያገኘነውን አንፃራዊ ሠላም ዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።
የሠላም ጥሪውን ተቀብለው በርካቶች እጃቸውን ለመንግሥት እየሰጡ መሆኑን የገለፁት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ሠላምን ፈልገው እጃቸውን የሚሰጡትን ኀይሎች ስልጠና እየሰጠን ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲሸጋገሩ እናደርጋለን ብለዋል።
ስለሆነም አሁንም ቢሆን በተሳሳተ መንገድ ተታለው ወደ ግጭት የገቡ እና የሌላ አካል ዓላማ ማስፈፀሚያ የሆኑ ኃይሎች መንግሥት የሰጠውን የሰላም ጥሪ ተጠቅመው እጃቸውን እንዲሰጡ አሳሳበዋል።
ለሠላም መስራት አማራጭ የሌለው ዋናው አጀንዳችን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ሠላምን ለማፅናት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው የክልላችንን ሰላም ለማጽናትና ሁሌም ሕግ እንዲከበር መሥራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። የሕዝባችንን ሠላም ለማስጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሠሩ ማድረግም ትኩረት ይሠጠዋል ብለዋል።
መረጃው የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ነው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!