
ሰቆጣ: ታኅሳስ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች መገኛ ሀገር ናት። ለዘመናትም አንዱ የአንዱን ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ቋንቋ እና እምነት እያከበሩ ተቻችለው ኑረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገጠሙ ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሰላምን ቀዳሚ ምርጫ ማድረግ እንደሚገባ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሃይማኖት አባቶች አሳስበዋል። የሃይማኖት አባቶቹ “ሰላሟ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ልናወርስ ይገባል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የዋግ ኽምራ ሀገረ ሥብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ኃይሌ ዓለሙ በቤተ ክርክትያን ያለሰላም የሚጀምር ትምህርት፤ ያለሰላም የሚቀደስ ቅዳሴ የላትም ነው ያሉት።
“ሰላም ለሁሉም” ብሎ እራሡ ክርስቶስ ያበሰረውን ሰላም እኛ ካህናቶችም ለሕዝቡ ሰላም፣ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ለመሪዎቿ ሰላም እንዲሠጥ እንጸልያለን፤ እናስተምራለን ሲሉ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮውን አስረድተዋል፡፡
ሰላም ከሌለ ሀገር፣ ሕዝብ እና ሃይማኖት አይኖርም ያሉት ሊቀ ኅሩያን የእምነቱ ተከታዮች በመቻቻል እና በይቅርባይነት ችግሮችን በማለፍ ሰላሟ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ልናወርስ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የሰቆጣ ከተማ የቁርዓን መምህር ሸህ መሐመድ አደም በበኩላቸው ነብያችን ስለ ሰላም ሲያስተምሩ “አትገዳደሉ፣ አንዱ በአንዱ ጸጋ ደስ ይበለው” ብለው አስተምረውናል ብለዋል። ሙስሊም ማለት ከምላሱ ጠንቅ፤ ከእጁ አመል የሌለበት ይሁን ብለው ስለ ሰላም አስተምረውናል ሲሉ ተናግረዋል። ወጣቶች ስለሀገራቸው ሰላም ዱዓ ሊያደርጉ ይገባል ያሉት ሼህ መሐመድ የሃይማኖት አባቶችን መልዕክትም ሊያደምጡ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!