
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ትምህርት ሚኒስትር እና ከሌሎች የሩሲያ የትምህርትና ምርምር ተቋማት የተውጣጡ ልኡካንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከልኡካኑ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል ያለውን የቆየ የትምህርትና ሥልጠና ትብብር እንዲሁም አሁን ላይ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየሆነ ያለውን የትምህርት ሥርዓት፣ መዋቅር እና ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ርብርብ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በመጪዎቹ ዓመታት የትምህርት ዘርፉን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎችን አብራርተዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሸኔ በበኩላቸው፤ የሩሲያ መንግስት በትምህርቱ ዘርፍ ለኢትዮጵያ እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
በሩሲያ ፌዴሬሽን ትምህርት ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትብብር እና ህዝብ ግንኙነት ኀላፊ ኡስማን አብዱልአዝቪክ በበኩላቸው፤ የሩሲያ መንግስት ከኢትዮጵ ጋር ያለውን የትምህርትና ሥልጠና ትብብር በማሳደግ ከፍ ወዳለ ደረጃ የማድረስ ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ኡሁን ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል በትግበራ ላይ ያለውን የትምህርትና ሥልጠና የመግባቢያ ስምምነት ማሻሻልና ማደስ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን የትምህርት ትብብር ለማደስ የሚከናወኑ ቀሪ ሥራዎች በዲፕሎማቲክ ቻናል በኩል ለመፈጸም ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት መድረሳቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!