የአካባቢን ሰላም በማረጋገጥ የበጋ መስኖ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የደቡብ ወሎ ዞን ገለጸ፡፡

40

ደሴ: ታኅሳሥ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ ስንዴ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት የቅድመ ዝግጅት ግምገማ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ እያካሄደ ነው።

በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት 30 ሺህ 748 ሄክታር መሬትን በበጋ ስንዴ ለማልማት መታቀዱን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ ገልጸዋል፡፡ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።

በኩታ ገጠም በመስኖ ስንዴ ልማት እንዲለሙ የተለዩ አካባቢዎች ላይ በቀጣይ 20 ቀናት ውስጥ በንቅናቄ በመሥራት ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራን በተመለከተ ተግባሩን ለመፈፀም የሰው ኀይል ልየታና የቅየሳ መሳሪያዎችን ጨምሮ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል በትኩረት መሥራት እንደሚገባም መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል።

በቀጣይም በዞኑ የሚገኘውን 116 ሺህ በላይ ኩንታል ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በተገቢው ለአርሶ አደሩ የማድረስ ሥራ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል፡፡

የሜካናይዜሽን እርሻን የማጠናከር ተግባርን ቁልፍ ሥራ አድርጎ በመያዝ የዞኑን የማምረት አቅም ማሻሻል ያስፈልጋልም ተብሏል።

የአካባቢን ሰላም በተገቢው መልኩ በማረጋገጥ የበጋ መስኖ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ላይ በትኩረት እና በላቀ ተነሳሽነት መሥራት እንደሚገባም የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ፊኒክስ ሀየሎም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዞኑ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም እየሠራ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleኢትዮጵያ እና ሩሲያ የትምህርት ትብብራቸውን ለማደስ የሚከናወኑ ቀሪ ሥራዎችን በዲፕሎማቲክ ቻናል በኩል ለመፈጸም ተስማሙ።