“እየጣልናቸው የመጣናቸውን እድሎች ለመሠብሠብ እና ለመጠቀም ተከታታይ ውይይቶች ያስፈልጋሉ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

108

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ መሪዎች በክልሉ ወቅታዊ እና መደበኛ ሥራዎች ዙሪያ ውይይት እያደረጉ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በቀውስ ውስጥም ኾነን መደበኛ ሥራዎችን ለማስቀጠል የሄድንበት ርቀት አበረታች ነበር ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ በመልእክታቸው የክልሉን ሕዝብ የሥነ ልቦና ልዕልና በተላበሰ መንገድ አመራሩ በአንድ እጃችን ከግጭት ለመውጣት በሌላ እጃችን ደግሞ መደበኛ ሥራዎቻችን ለማስቀጠል ብርቱ ጥረት ተደርጓል ብለዋል። በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መገኘቱንም አንስተዋል።

ከነባራዊ ሃቁ የራቁ የግጭት እና ጦርነት መረጃዎች በሚናፈሱበት ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ምክክሮችን ማካሄዳችን የበርካቶችን አስተሳሰብ ቀይሯል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት ትክክለኛ ገጽታ ያመላከተም ነበር ብለዋል።

አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት የሚያስችል ተከታታይ ምክክር ያስፈልጋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “እየጣልናቸው የመጣናቸውን እድሎች ለመሰብሰብ እና ለመጠቀም ተከታታይ ውይይቶች ያስፈልጋሉ” ብለዋል።

በተለይም የመንግሥት ሠራተኛውን ከየተቋሙ ተልዕኮ ጋር አገናኝቶ አገልጋይነቱን እና ኀላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። የውይይቱ ዓላማም ነባራዊ ሃቁን ማስረዳት፣ የጋራ መግባባት መፍጠር እና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ማስገባት ነው ብለዋል።

በውይይቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፍዬ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ የቢሮ ኀላፊዎች እና ምክትል ቢሮ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ333 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።
Next articleበዞኑ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም እየሠራ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና መምሪያ አስታወቀ።