ከ333 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።

23

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016 ዓ.ም ከ333 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል። ቢሮው በበጀት ዓመቱ የመስኖ ልማት የዝግጅት እና የትግበራ ሥራዎች ላይ ከዞን እና ከወረዳ የግብርና አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር እየተወያየ ነው።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) “ግብርናችን ለኢኮኖሚያችንም ኾነ ለሰላማችን መሰረት ነው” ሲሉ ገልጸዋል። የግብርው ዘርፍ ሲያድግ የአርሶ አደሮች ሕይዎት የተሻለ ይኾናል፤ ወጣቶችም የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው የተሻለ ኢኮኖሚ ያንቀሳቅሳሉ ሲሉ አብራርተዋል።

ግብርናው የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ተከትሎም የተሻለ ሰላም ይሰፍናል፤ የተሻሉ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዲፈጠሩም እድል ይሰጣል ብለዋል ቢሮ ኀላፊዉ። አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አማራ ክልል የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም አንስተዋል።

ቢሮው የግብርና ግብዓቶች በተለይም የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በወቅቱ እንዲደርስ ጠንካራ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም ዶክተር ድረስ ተናግረዋል። የግብርና ግብዓቶች በቅልጥፍና መጓጓዝ እንዲችሉ በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች እና መላ ሕዝቡ መተባበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የመስኖ ሥራን ከምንጊዜውም በላይ በርትቶ በማከናዎን ለክልሉ ሕዝብ ኢኮኖሚ ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል። ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ቤተሰቦች አርሶ አደሮችን የመደገፍ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመዘዋወር በመሥኖ ሥራ ላይ ለሚሰማሩ አርሶ አደሮች እና ባለሙያዎች ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል። 333 ሺህ ሄክታር መሬት በመጀመሪያ ዙር መስኖ ይሸፈናል፤ 114 ሺህ ሄክታር የሚኾነው ደግሞ በሁለተኛ ዙር ዳግም ይለማል ነው ያሉት። በሁለቱም ዙር የመስኖ ልማት 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም አመላክተዋል።

አጠቃላይ በመስኖ ከሚለማው ማሳ 250 ሺህ ሄክታሩ በስንዴ ሰብል እንደሚሸፈንም ተናግረዋል። ለበጋ ስንዴ ልማት የተሰጠው ትኩረት በክልሉ ለሚገኙ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በቂ ግብዓት ከማቅረብ በተጨማሪ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ምክትል ቢሮ ኀላፊው በየአካባቢው የሚገኙ ወንዞችን እና ነባር የመስኖ አውታሮችን ከመጠቀም በተጨማሪ እና የውኃ መሳቢያ ፓንፖችን የማሰራጨት ሥራ እየተሠራ ሥለመኾኑም ተናግረዋል።

ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች የተውጣጡ የግብርና የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎችም በየአካባቢያቸው ያለውን የመስኖ ልማት አቅም በመለየት ከአርሶ አደሮች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ፈጥረው በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

በአሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፀደይ ባንክ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን አስጀመረ።
Next article“እየጣልናቸው የመጣናቸውን እድሎች ለመሠብሠብ እና ለመጠቀም ተከታታይ ውይይቶች ያስፈልጋሉ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ