“ከባሕር ዳር – ወልዲያ ያለውን የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት በዚህ ዓመት አጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ እየሠራን ነው” የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

59

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከባሕር ዳር – ወልዲያ ያለውን ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በአጠቃላይ ከባሕር ዳር – ወልዲያ – ኮምቦልቻ ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክትን በሁለት የግንባታ ምዕራፍ ከፍሎ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑም ተመላክቷል፡፡

የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ከባሕርዳር እስከ ወልዲያ የሚደርሰውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ያጠቃልላል። ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከወልዲያ እስከ ኮምቦልቻ ድረስ ያለውን እንደሚሸፍን ተገልጿል፡፡

የመጀመሪያውን የግንባታ ምዕራፍም በተያዘው በጀት ዓመት አጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክቱ ሪዚደንት ሀብታሙ ተሾመ (ኢ.ር) ያስታወቁት፡፡

ከባሕርዳር እስከ ወልዲያ እንደሚተከሉ ከሚጠበቁት 640 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች መካከልም 620 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ተከላ ተጠናቅቋል ብለዋል፡፡ ቀሪ ምሰሶዎችን ለመትከል የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ከባሕርዳር እስከ ወልዲያ የኮንዳክተር ገመድ ለመዘርጋት ከታሰበው 295 ነጥብ 87 ኪሎ ሜትር ውስጥ 222 ኪሎ ሜትር ማጠናቀቅ መቻሉንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግብፅ ወደ ስምምነት እና ትብብር የሚደረገውን ጉዞ ተቃውማ መንገድ ዘግታለች” የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next article“በውኃ ድርሻ ላይ መግባባት ባለመኖሩ 4ኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ድርድር ያለስምምነት ተጠናቅቋል” የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን መሪ አምባሳደር ስለሽ በቀለ