
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ አራተኛው ዙር የሦስትዮሽ ድርድር ዙሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫው ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን አራተኛውን ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ላለፉት 3 ቀናት በአዲስ አበባ ማካሄዳቸውን ገልጿል። እነዚህ አራት ዙር ድርድሮች የተካሄዱት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና በግብጹ ፕሬዝዳንት ዓብዱል ፋታህ ኤል ሲሲ የጋራ መግባባት መሆኑን አስታውሷል።
ሁለቱ መሪዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ አሞላል እና ዓመታዊ ሥራን አስመልክቶ የወጣውን ደንብና መመሪያ አጠናቅቆ ለማስቀጠል አስፈላጊው ሁሉ ጥረት እንዲደረግም ጥረዋል። ይህ ለአራት ዙር የዘለቀው ድርድር ሦስቱ ሀገራት በመካከላቸው ያሉ ዋና ዋና ልዩነት ፈጣሪ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት እንዲያደርጉ ማገዙም እንደማይዘነጋ መግለጫው ጠቁሟል።
በእነዚህ አራት ዙሮች ኢትዮጵያ ከሁለቱ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ዋና ዋና ልዩነቶችን ለመፍታት እና የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት አድርጋለች። በአንፃሩ ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቧን ይዛ በመቀጠል ወደ ስምምነት እና ትብብር የሚደረገውን ጉዞ ተቃውማ መንገድ ዘግታለች ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ አሞላል እና ዓመታዊ አሠራር መመሪያ እና ደንቦች ላይ የተደረገው ድርድር በሦስቱ ሀገራት መካከል መተማመን ለመፍጠር እንጂ በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ የኢትዮጵያን መብት ለመንጠቅ ያለመ አይደለም፤ ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን በፍትሐዊነት እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ ላይ በመመሥረት የአሁንና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል በግልፅ ማሳወቅ ትፈልጋለችም ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።
እ.አ.አ 2015 ሦስቱ ሀገራት የተፈራረሙት የመርህ ስምምነት ለዚህ ድርድር መሰረት ነው ያለው መግለጫው ከዚህም በላይ ከ2020 ጀምሮ ጉዳዩን የያዘው የአፍሪካ ኅብረት ሦስቱ ሀገሮች በሰላማዊ መንገድ ወደ መፍትሔ ሀሳብ እንዲመጡ ዕድል የሚፈጥርበትን መድረክ ማመቻቸቱን አስታውሷል።
ላለፉት 3 ቀናት የተካሄደው አራተኛው ዙር ድርድር ከተጠናቀቀ በኋላ ግብፅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር እና የአፍሪካ ኅብረት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌን የሚጻረር መግለጫ አውጥታለች ያለው መግለጫው ኢትዮጵያ በግብፅ በኩል የቀረበባትን የተሳሳተ መረጃም አትቀበልውም ብሏል።
ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ እና በፍትሐዊ ድርድር የሦስቱን ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ የመፍትሔ ሀሳብ ላይ ለመድረስ ያላትን ቁርጠኝነት ይዛ እንደምትቀጥልም ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!