
ደሴ፡ ታኅሳሥ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በከተማ አሥተዳደሩ የተሻለ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መኖሩን የደሴ ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል።
በደሴ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማጠናከር እና የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የከተማዋ ከንቲባ ኮሚቴ አባላት በገራዶ እና ጀሜ የኢንዱስትሪ መንደሮች በመገኘት ምልከታ አድርገዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ በመግባት ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸው ተመልክቷል። የተወሰኑት ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራ ሳይገቡ መቆየታቸው በምልከታው ተረጋግጧል።
አሚኮ ያነጋገራቸው አልሚዎችም ከመሠረተ ልማት፣ ከብድር እና ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተያያዙ ችግሮችን አንስተዋል።
የደሴ ከተማ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አቶ አለባቸው ሰይድ በከተማዋ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በመነቃቃት ላይ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ በአምስት ወር ብቻ 89 ባለሃብቶች በከተማዋ ኢንቨስት ማደረጋቸውን ተናግረዋል።
የመሠረተ ልማት ችግሮች መቀረፋቸውን የተናገሩት ኀላፊው ብድርን በተመለከተ ለተነሱ ችግሮች በባንኮች በኩል እንደሚፈታ እና ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ ከክልል እና ከፌደራል ጋር በመኾን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በርካታ አልሚዎች በገቡት ውል መሠረት ወደ ሥራ በመግባት ምርት እና አገልግሎት በመስጠት የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸው አበረታች ነው ብለዋል። በልዩ ልዩ ሰበቦች ወደ ሥራ ያልገቡም ከችግራቸው በመውጣት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲገቡ አሳስበዋል።
የኮሚቴውን ምክረ ሀሳብ ችላ በማለት ወደ ሥራ የማይገቡ ባለሃብቶችን ግን መመሪያውን መሠረት በማድረግ ቦታው ለሌሎች አልሚዎች የሚተላለፍ ይኾናል ተብሏል።
ዘጋቢ ፡- አንተነህ ፀጋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!