“ቦርዱ ነጻነቱን እና ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲወጣ እሰራለሁ” ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ

37

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነጻነቱን እና ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲፈጽም በቁርጠኝነት ለመሥራት መዘጋጀታቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ኾነው የተሾሙት ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብስባው ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲኾኑ ከመንግሥት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።ወይዘሮ ሜላተወርቅ ቦርዱን ለመምራት በሕዝብ እና በመንግሥት የተሰጣቸውን የሥራ ኀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ሰብሳቢዋ ቀደም ሲል የቦርዱን አፈጻጸም ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች እንደነበሩ አስታውሰው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒ ኾኖ መጠናቀቁ ለዚያ ማሳያ ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ በደቡብ ክልል የአደረጃጀት ሕዝበ ውሳኔዎች በተሳካ ሁኔታ መከናወናቸው የተቋማዊ ለውጡ ውጤት መኾናቸውንም ነው የገለጹት።

የቦርዱን ስኬቶች በማስጠበቅ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቀጥል፤ በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነት ለመጨመር ከሌሎች አመራሮች ጋር በትጋት እንደሚሰሩም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
ቦርዱ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ ቢኾንም፤ የሕዝብን ፍላጎት ከማርካት አኳያ የሚነሱ ክፍተቶችን መፍታትም ቀዳሚ ሥራቸው እንደሚሆን አመልክተዋል።
በቦርዱ አሰራር ላይ ቅሬታ ያለው ማንኛውም አካል በተዘጋጁ የጥቆማ መስጫዎች ጥቆማ እንዲሰጥም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው አዲሷ ተሿሚ ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ መኾናቸውን፤ እንዲሁም ከትምህርት ዝግጅት እና ከሥራ ልምድ አኳያ ቦርዱን ለመምራት ብቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ሰብሳቢዋ ሕዝብ እና መንግሥት የጣለባቸውን ኀላፊነት በብቃት እና በታማኝነት ሊወጡ እንደሚገባም ነው አባላቱ ያሳሰቡት።ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፤ በሰላም እና ደህንነት ጥናት ሁለተኛ ዲግሪ፤ እንዲሁም በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

በተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት በባለሙያነት እና በኀላፊነት ያገለገሉት ወይዘሮ ሜላተወርቅ ከየካቲት 2012 ዓ.ም እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጽህፈት ቤት ኀላፊ በመኾን አገልግለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበድርቅ ምክንያት የቀነሰውን የማር ምርት መልሶ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
Next article“ኢትዮጵያ ከስፔን ጋር ያላትን ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ ደረጃ ለማሳደግ ፍላጎት አላት” አቶ ደመቀ መኮንን