
ሰቆጣ: ታኅሳሥ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ወይዘሮ ሙሉ አፈወርቅ በድሃና ወረዳ አምደወርቅ ከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው ። አርሶ አደር ሙሉ ባሏቸው 15 ባሕላዊ እና 5 ዘመናዊ ቀፎዎችን በመጠቀም ቤተሰቦቻቸውን ያሥተዳድራሉ፤ ልጆቻቸውንም ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡
ከአንድ ባሕላዊ ቀፎ እስከ 15 ኪሎ ግራም ማር አገኝ ነበር ያሉት አርሶ አደር ሙሉ በዘንድሮው ዓመት ግን በአማካኝ ከ8 እስከ 10 ኪሎ ግራም ብቻ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ የማር ምርት መቀነስ ዋነኛው ምክንያት በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ድርቁ የፈጠረው ችግር በንብ ሃብታቸው ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑንም ተናግረዋል።
የድሃና ወረዳ እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የንብ እርባታ ባለሙያው ሽፈራው አሸንፍ በወረዳው ከ15 ሺህ በላይ የንብ መንጋ እንዳለ ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት 183 ቶን የማር ምርት ይገኛል ተብሎ ቢታቀድም 70 ቶን ማር ብቻ መገኘቱ ተናግረዋል፡፡ በወረዳው የተከሰተው የዝናብ እጥረት በማር ምርቱ ላይ ተጽዕኖ ማድረሱንም አንስተዋል፡፡ በወረዳው በሥፋት አገልግሎት ላይ የሚውለው የፀረ አረም ኬሚካልም በማር ምርቱ ላይ ተፅዕኖ ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመነጋገር በድርቅ ምክንያት የቀነሰውን የማር ምርት መልሶ ለማሳደግ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲሳይ አያሌው በዘንድሮው ዓመት እንደብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ የማር ምርት ለማግኘት መታቀዱን እና 9 ሺህ ኩንታል ማር ብቻ መሰብሰቡን አንስተዋል፡፡
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በማር ምርት የሚታወቁት ዝቋላ፣ ስሃላ ሰየምት እና አበርገሌ ወረዳዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት የማር ምርታቸው እንደቀነሰም ገልጸዋል፡፡
መጭው የበጋ ወቅት ለንብ እርባታ አዳጋች ይኾናል ያሉት አቶ ሲሳይ ማኅበረሰቡ የሥኳር፣ የፓፓዬ እና ሰብል ምርትን ለንቦች በመመገብ እና አካባቢያቸውን በማጽዳት መንከባከብ እንዳለበት መልእክት አስተላልፈዋል። በተለይ የከፋ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ አናቢዎች ቀፎዎችን ወደ አጎራባች አካባቢዎች ሊያስጠጉ እንደሚገባ ኀላፊው አሳስበ።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!