“የወባ ስርጭትን ለመከላከል የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን ዘላቂነት ባለው መንገድ መሥራት ይገባል” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)

40

“የወባ ስርጭቱ ዘንድሮ 50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የዚህ ዓመት የወባ ስርጭት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 50 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ክልላዊ የወባ ሳምንት የማኅበረሰብ ንቅናቄ መድረክን አካሂደዋል። ኢትዮጵያ በዓለም በወባ ከሚጠቁ ሀገራት አንዷ መኾኗ በውይይቱ ተነስቷል። የአማራ ክልልም 80 በመቶው ወባማ እንደኾነ ነው የተገለጸው።

80 በመቶ የሚኾነው ሕዝብ ደግሞ ለወባ ተጋላጭ ነው። ምዕራቡ የክልሉ አካባቢ ደግሞ 91 በመቶ የሚኾነው ለወባ ተጋላጭ እንደኾነ ተነስቷል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 30 ወረዳዎች የክልሉን 73 ነጥብ 6 በመቶ የወባ ስርጭት ይሸፍናሉ ተብሏል። ባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር፣ ምዕራብና ምሥራቅ ደምቢያ፣ ፎገራ፣ ሊቦ ከምከም፣ በለሳ እና የመሳሰሉ ወረዳዎች ከቀዳሚዎች ውስጥ ይካተታሉ።

በኢንስቲትዩቱ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ዳምጤ ላንክር በአማራ ክልል በ2016 በጀት ዓመት እስከ ታኅሣሥ የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ ከ671 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ ተይዘዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲታይ 50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የ15 ሰዎች ሕይዎትም ማለፉንም አቶ ዳምጤ የገለጹት።

በበጀት ዓመቱ 651 ቀበሌዎችን የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ታቅዶ በተለያዩ ምክንያቶች መሸፈን የተቻለው 37 በመቶ ብቻ ነው። የአየር ጸባይ መለዋወጥ፣ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መቋረጥ፣ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀም፣ የወባ ኬሚካል አቅርቦት እጥረት ለወባ ሥርጭት መጨመር በምክንያትነት ተነስተዋል።

በተለያዩ ችግሮች የጤና ተቋማት ከመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች መድኃኒት በወቅቱ አለመውሰድ እና ድርጅቶችም ወደ ተቋማት አለማድረስ ችግሮች እንደነበርም ተነስቷል።
በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ወባን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት አስቸጋሪ እንዳደረገው ተሳታፊ የጤና ባለሙያዎች አንስተዋል። እንደሌሎች በሽታዎች ትኩረት አለመስጠት ችግር እንዳለም ተነስቷል።

የታመሙ ሰዎችን ለማከም የግብዓት መቆራረጥ ችግር እንዳለም ተገልጿል። የአጎበር አጠቃቀም ችግር መኖርን እና በጸጥታ ችግር ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አለመቻሉን ተሳታፊዎች አንስተዋል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ሀገሪቱ ለወባ በሰጠችው ትኩረት ለዓመታት ወባን መቆጣጠር ቢቻልም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አሳሳቢ እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል። ስርጭቱን ለመከላከል የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን ዘላቂነት ባለው መንገድ መሥራት ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአዲስ የተመረጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ማን ናቸው?
Next articleበድርቅ ምክንያት የቀነሰውን የማር ምርት መልሶ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።