
ታኅሳሥ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ የተወለዱት በጎንደር ከተማ ነው።
በትምህርት ዝግጅታቸው የመጀመሪያ ዲግሪ በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በሰላም እና ደኅንነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ተጨማሪ ሁለተኛ ዲግሪ በሕዝብ አሥተዳደር ከሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።
በሥራ ልምዳቸው በኢትዮጵያ የጉምሩክ ባለሥልጣን ከጀማሪ የሕግ ባለሙያነት እስከ ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ የሕግ አፈጻጸም መምሪያ በመኾን አገልግለዋል።
ኒውጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን በማቋቋም የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻውን በመምራት ውጤታማ አድርገዋል፤ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የሴኔት አባል በመኾንም አገልግለዋል፡፡
የግል የሕግ አማካሪ ተቋም በማቋቋም የሥልጠና እና የማማከር አገልግሎት፣ የሕግ ሰነዶች ዝግጅት፣ ግልግልና የግልግል አገልግሎት እንዲሁም ለሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የስትራቴጂና የፖሊሲ ሰነዶችን በመቅረጽ ሰፊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡
ከየካቲት 2012 ዓ.ም እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመኾን ከቦርድ አመራሮችና ከመላው ሠራተኛ ጋር በመኾን ምርጫ 2013 ተሳትፈዋል። ኢፕድ እንደዘገበው በክልሎች የተካሄዱ ሕዝበ ውሳኔዎችንም በብቃት የመሩና በምርጫ ቦርድ የሪፎርም ሥራዎች በብቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!