
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ እና የዋጋ ንረትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ ልዩ ትኩረት መሥጠቱን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ድኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ.ር) ባቀረቡት ሪፖርት ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም፣ የሃብት አጠቃቀም፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የፖሊሲ ዝግጅት፣ የክትትል እና ግምገማ ሥርዓት ውጤታማነትን ለማጎልበት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አብራርተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም የተቋማት ዘርፍ ተኮር የአንድ እቅድ አንድ ሪፖርት የአሠራር ሥርዓት ውጤታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን በሚመለከት ማብራሪያ ጠይቀዋል።
በጥያቄቸውም የሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ደረጃ እና ለክልሎች የልማት ዕቅድ የሚደረገውን ድጋፍ እና ክትትል ያለበትን ሁኔታ አንስተዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) በሰጡት ምላሽ መንግሥት የ10 ዓመት የልማት ዕቅዱን ለማሳካት ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በብዝኃ ዘርፍ የዕድገት ምንጮች ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት በተደረገ ግምገማ ውጤት መምጣቱንም አብራርተዋል።
ለአብነትም በግብርና ዘርፍ ትኩረት በተሰጣቸው የሰብል፣ የእንስሳት፣ የዓሳ ሃብት ልማት እና የአካባቢ እና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች እድገት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በውጪ ንግድ እና በሥራ እድል ፈጠራ የተያዘው ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ጉድለት መታየቱን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ለዕቅዶች አለመሳካት ምክንያት መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም ጉድለቶቹን ለማካካስ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሠጥ አንስተዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ እና የዋጋ ንረትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ ልዩ ትኩረት መሥጠቱንም ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።
የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓቱን ቀጣይነት ባለው መልኩ በመምራት ሀገራዊ እድገትን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ለዚህም የተቋማትን የአንድ እቅድ አንድ ሪፖርት የአሠራር ሥርዓት በተገቢው መልኩ ተግባራዊ እንዲኾን ጠንካራ የድጋፍ እና ክትትል ሥራ ማከናዎን እንደሚገባ አጽንኦት ሠጥተዋል።
ክልሎች በሀገራዊ የልማት እቅድ ስኬት አዎንታዊ ሚና እንዲኖራቸው መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!