“ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መቃኘት ያስፈልጋል” የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህር

53

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ብሔራዊ ምክክርን በርካታ ሀገራት ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እና ብሔራዊ ማንነትን ለመገንባት ተጠቅመውበታል። ሀገራዊ ምክክር የሃሳብ ልዩነትን ወደ ተቀራረበ መንገድ ለማምጣትም ሚናው የጎላ ነው።

ምክክር በማኅበረሰብ ደረጃ የሚከሰቱ ቅራኔዎችን ለመፍታት ሊካሄድም ይችላል፡፡ ከዚህም ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ለውጥ (ፖለቲካል ሪፎርም)፣ ሕገ መንግሥትን ለማሻሻል ኾነ ለመቀየር እና ለረጅም ጊዜ ሥር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ የሰላም ግንባታ ለማምጣት ሊካሄድ እንደሚችል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ያየው ገነት ገልጸዋል።

ብሔራዊ ምክክር አካሂደው ከገጠማቸው ችግር የወጡ እና በተከተሉት የተሳሳተ አካሄድ አሁንም ድረስ ከችግር ያልተላቀቁ ሀገራትን በማሳያነት አንስተዋል።
ቱኒዝያ የአረብ ጸደይ አብዮትን ተከትሎ ያጋጠማትን ችግር ለመፍታት የተሳካ ምክክር ከአካሄዱ ሀገራት መካከል በምሳሌነት የምትጠቀስ ሀገር ናት። በሀገሪቱ ገለልተኛ ሲቪክ ማኅበራት መኖራቸው እና ኀላፊነት ወስደው መሥራታቸው ለስኬቱ በምክንያትነት ተቀምጧል፡፡

ምክክሩ በቱኒዚያ ማኅበረሰብ ተቀባይነት እና እምነት በማግኘቱ፣ ተሳታፊዎች በቅንነት እና በታማኝነት በመሥራታቸው ለስኬቱ ሌላው ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህም አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱን መቀየር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በሌላ መንገድ የመን ደግሞ ያልተሳካ ምክክር ከአካሄዱ ሀገራት ተርታ ተቀምጣለች። ለዚህ ደግሞ የሲቪክ ማኅበራት ደካማ መኾን እና በምክክር ሂደቱ የነበሩ ተሳታፊዎች አመራረጥ ላይ ችግር መኖሩ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ዝቅተኛ መኾን እና አብላጫው ደቡባዊ የመን በምክክሩ ባለመሳተፉ ምክክሩ ሳይሳካ ቀርቶ ሀገሪቱ ወደ ለየለት የፖለቲካ ቀውስ እንድትገባ ኾኗል፡፡ እስከ አሁንም የየመን ችግር እልባት አለማግኘቱን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እና የጋራ ብሔራዊ ማንነትን ለመገንባት ምክክር ዋነኛ መፍትሄ እንደኾነ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የተሳካ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ደግሞ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መቃኘት እንደሚያስፈልግ መምህሩ መክረዋል።

በተለይም ደግሞ ምክክሩ ሕዝባዊ ድጋፍ እንዲኖረው መሥራት ያስፈልጋል። በሀገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶችን መፍታት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም አንስተዋል። ተመጣጣኝ የማኅበረሰብ ውክልና መኖር እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

በምክክር ሂደቱ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ግልጽነት ያላቸው እና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው ሊኾኑ ይገባል ነው ያሉት። የሚወሰኑ ውሳኔዎች እንዴት እንደሚፈጸሙ በግልጽ የሚያሳይ መኾን አለበት። የምክክር አወያዮች እና ሲቪክ ማኅበራት ገለልተኛ በመኾን ሥራቸውን ማከናወን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት አምስት ወራት ለ24 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩን የደቡብ ወሎ ዞን ሥራና ስልጠና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleኢትዮጵያ እና ሩሲያ በቴክኖሎጂ የታገዘ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ሊኖራቸው እንደሚገባ ተገለጸ።