ባለፉት አምስት ወራት ለ24 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩን የደቡብ ወሎ ዞን ሥራና ስልጠና መምሪያ አስታወቀ።

32

ደሴ: ታኅሳስ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደቡብ ወሎ ዞን ሥራና ስልጠና መምሪያ የባለፈው ዓመት የእቅድ አፈጻጸም እና የ2016 በጀት ዓመት የእቅድ ግምገማ አካሂዷል።

መምሪያው ከሥራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት አባላት፣ ከወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እና ከኮሌጅ አመራር አባላት ጋር በጋራ በመኾን በበጀት ዓመቱ የአምስት ወር እቅድ አፈፃፀምን ገምግሟል።

በበጀት ዓመቱ የዞኑን ልማት ለማፋጠን የሚያስችሉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር እቅዶች በመተግበር ላይ መኾናቸው ተነስቷል። በእቅዱ ላይ ትኩረት ከተሰጡባቸው እና እየተሠራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች ውስጥ የወጣቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ የሴቶች፣ ከስደት ተመላሾች፣ የአካል ጉዳተኞች ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማት እና የሥራ እድል ፈጠራ ሥራዎችም ይገኙበታል።

የደቡብ ወሎ ዞን ሥራና ስልጠና መምሪያ ኀላፊ ደምስ እንድሪስ እንዳሉት በ2015 ዓ.ም ለ136 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል እደተፈጠረላቸው አስረድተዋል። በክልሉ ካሉ ዞኖች ጥሩ አፈፃፀም መኾኑንም ተናግረዋል።

በባለፈው በጀት ዓመት ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ለሥራ እድል ፈጠራ መዋሉንም አስረድተዋል። መምሪያ ኀላፊው ባለፉት አምስት ወራት በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ለሚገኙ ለ24 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩንም ጠቁመዋል።

የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ይገባል ያሉት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን ለዚህም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። በመድረኩ በበጀት ዓመቱ ጥሩ አፈፃፀም ላመጡ ወረዳና ከተማ አሥተዳደሮች የእውቅናና ምሥጋና ፕሮግራም ተካሂዷል።

ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ጌትነት ታደሰ የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኾነው ተሾሙ።
Next article“ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መቃኘት ያስፈልጋል” የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህር