
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን እና የወረታ ኢንተርናሽናል ባለቤት አቶ ታደሰ ምህረቴ በአማራ ክልል በድርቅ ለተጎዱ እና ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ ወገኖች 10 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አድርገዋል።
ድጋፉ በሰሜን ጎንደር፣ በዋግኽምራ እና በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ወገኖች የሚደርስ ነው ተብሏል። የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው በድጋፍ ርክክቡ ላይ እንደተናገሩት በአማራ ክልል ከ600 ሺህ በላይ ለሚኾን ሕዝብ አስቸኳይ የዕለት ምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ከክልሉ መረጃ አግኝተናል ብለዋል።
የበላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን መሥራች እና ባለቤት በላይነህ ክንዴ ለነዚህ ወገኖች ለሚደረገው አስቸኳይ ድጋፍ በራሳቸው ተነሳሽነት የ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድጋቸውን ገልጸዋል። “ወገኖቻችንን እኛው መደገፍ አለብን፤ አስፈላጊውን እህል ገዝተን በራሳችን ማጓጓዣ በየቦታው እናደርሳለን ብለዋል።
የወረታ ኢንተርናሽናል ባለቤት አቶ ታደሰ ምህረቴም የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል። ለእነዚህ ወገኖች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በግንባር በመገኘት እንደሚያደርሱ ገልጠዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ.ር)፣ የደብረ ብርሃን ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ እንዲሁም የዋግ ልማት ማኅበር አዲስ አበባ ማስተባበሪያ አቶ ምትኩ በየነ ሲሆኑ ባለሃብቶቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ለወገናቸው ባሳዩት አለኝታነት አመስግነዋል።
ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ድርቁ ወደ ረሃብ ከመሸጋገሩ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እየደረሰ ነው። ሁሉም ወገን ወዳድ ኢትዮጵያዊያን አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
በሰሜን ጎንደር 390 ሺህ፣ በዋግኽምራ 290 ሺህ እና በደብረ ብርሃን ከ77 ሺህ በላይ አስቸኳይ የዕለት ድጋፍ የሚሹ ወገኖች እንዳሉም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!