“ወደ ስህተት የሚመራንን የሀሰት ወሬ አንሰማም፤ የሰላም ጀግኖች ኾነን ሕዝባችንን እንክሳለን” የሸዋ ሮቢት ማዕከል የተሃድሶ ሠልጣኞች

31

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሸዋ ኮማንድ ፓስት ለ10 ቀናት ለ3ኛ ዙር የተሃድሶ ሥልጠና ሲከታተሉ የቆዩ 161 ሠልጣኞች ተመርቀዋል።

የተሃደሶ ሥልጠናውን የተከታተሉት በሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አሥተዳደር እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ታራሚዎች ናቸው።
ታራሚዎች በክልሉ ተከስቶ በነበረው ግጭት፣ ሁከት እና ብጥብጥ “ተሳትፈዋል” በሚል ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ሥር የቆዩ ናቸው።

ሠልጣኞቹ በማዕከሉ ቆይታቸው “ሰላም ለሁላችን፣ ሚናችን ለሰላማችን፣ የሰላም ምንነት፣ የሰላም አስፈላጊነት፣ ከግጭት እና ከጦርነት መውጫ መንገድ ከተሃድሶ ሠልጣኞች ምን ይጠበቃል” በሚሉ ርዕሶች ላይ የተዘጋጀውን ሥልጠና ወስደዋል። ከ161 ተመራቂዎች መካከል አምስቱ ሴቶች ናቸው።

ተመራቂዎቹ በማረሚያ ቤቱ ቆይታ ያሳዩት ሥነ ምግባር ጨዋነት የተሞላበት እንደነበር ተገልጿል። ወደ ኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ለአካቢያቸው ሰላም በኀላፊነት እንዲሠሩ መልእክት ተላልፏል።

ሠልጣኞቹ በሰጡት አስተያየት በማኅበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ በመታለል በስሜታዊነት ወደ አመጽ መግባታቸውን ተናግረዋል። “ወደ ስህተት የሚመራንን የሀሰት ወሬ አንሰማም፤ የሰላም ጀግኖች ኾነን ሕዝባችንን እንክሳለን” ሲሉም ተናግረዋል። በዚህ ሥልጠና ውስጥ በማለፋቸው የተደሰቱ መኾኑን እና ከዚህ እንደወጡ የሰላም አምባሳደር እደሚሆኑ ገልጸዋል።

ከኅብረተሰቡ ጋር በሚቀላቀሉበት ወቅት ሌሎች ወጣቶች እንዳይታለሉ ለማስተማር ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል። በማዕከሉ የተሰጠው ሥልጠና በተለይ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እና የሰሜን ሸዋ ዞን ታራሚዎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ መረዳዳትን እንዲያዳብሩ እና የቆየውን የተዛባ ትርክት እዲያርሙ እድል የሰጠ እንደነበር ሠልጣኞች ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል፡፡
Next articleከ40 በላይ የቻይና አምራች ኩባንያዎች የተሳተፉበት የኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ።