
ጎንደር: ታኅሳስ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት ዙሪያ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከፀጥታ አካላት ጋር በጎንደር ከተማ ውይይት እያደረገ ነው።
በውይይቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ለሰላም እና እርቅ የሚደረጉ ጥረቶች ስኬታማ የሚኾኑት በመተማመን፣ በመተባበር እና በመነጋገር ነው ብለዋል። ለዚህም የፀጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች እና አጋር አካላት የበኩላቸውን ሚና ሲወጡ መኾኑን አንስተዋል።
ሁሉም ሃይማኖቶች የጋራ የኾኑ መሠረታዊ የሰላም መገንቢያ አስተምህሮት እና እሴቶች አሏቸዉ ያሉት አቶ ደጀኔ “በአንተ ላይ እንዲኾን የማትፈልገውን በሌሎቹ ላይ አታድርግ” የሚለውን ሃይማኖታዊ አስተምሮት መተግበር ለሰላም እሴት ግንባታ ፋይዳው የጎላ መኾኑን አንስተዋል።
ይህን እና መሰል ወርቃማ ሕጎችን የሃይማኖት አባቶች በዘር፣ በፆታ እና በቀለም ሳይለዩ ለማኅበረሰቡ እንዲያስተምሩ ጠይቀዋል።”ሕጻናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች አና አዛውንቶች ሰላም ይፈልጋሉ፤ ለዚህ ደግሞ የፀጥታ ኃይሉ በትኩረት ይሠራልም” ነው ያሉት።
መገናኛ ብዙኀን ለሰላም ግንባታ ትልቁን ድርሻ የሚዎስዱ በመኾኑ ሚዲያዎች ግጭት ቆስቋሽ ከኾነ ተግባር መቆጠብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።በምክክሩ ሃሳብ የሰጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሀገር የምትገነባው የመነጋገር፣ የመቻቻል እና የውይይት ባሕልን ማሳደግ ሲቻል በመኾኑ ከግጭ አዙሪት መውጣት እና መወያየት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ልጆቻችን ከመገዳደል እንዲወጡ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም አስረድተዋል። እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ኀላፊነት መወጣት ሲችል ሀገር ትገነባለችም ብለዋል። ይህ እንዲኾንም የሰላም እና ግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አንስተዋል።
ዘጋቢ፡- አዲስ ዓለማየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!